መክሊት ሐደሮና ከለላ ሚዛነ ክርስቶስ፡ እያንፀባረቁ ያሉት ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች

የተወለዱበትን ቀዬ ለቆ፣ ባህልና አኗኗር ዘዬ፣ ዘመድና ቤተሰብ ትቶ መሰደድ ምን አይነት ስሜት ይኖረው ይሆን?

አገራቸው በጦርነት ፈራርሶ፣ ቤታቸው በጦርነት ወድሞ፣ በፖለቲካ እምነታቸው ተሳዳጅ ሆነው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ነገን በማለም የነጎዱትን ታሪክ ይቁጠራቸው።

ሃብቴን፣ ንብረቴን፣ ጨርቄንና ማቄን ሳይሉ ብዙዎች ተሰደዋል፤ ሜዳ ላይ ቀርተዋል፣ ጥሙ ረሃቡና መራቆቱ ሳይበግራቸው ባሕርና ተራሮችን ሲያቆራርጡ፤ ባሕር በልቷቸዋል አልያም እንደወጡ ላይመለሱ የቀሩትም በርካቶች ናቸው።

ኢትዮጵያውያን ወደ ሌላ አገራት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ያጠኑ ሰዎች እንደሚሉት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሕዝብ ስደት የተጀመረው በደርግ ወቅት ነው ይላሉ።

የተለያዩ አፍሪካ አገራት በተለይም ሱዳን የብዙዎች መቀመጫ ነበረች፤ ከዚያም ነገን ተስፋ ወደ ፈነጠቁላቸው የምዕራቡ አገራት አቅንተዋል።

ምንም እንኳን ካደጉበት አገር ባህል መነቀል ቀላል ባይሆንም በህይወት የተረፉ ስደተኞች ከዜሮ ጀምረው ኑሮን መስርተዋል፤ ልጆቻቸውን አሳድገዋል፣ ለቁም ነገርም አብቅተዋል።

ይህ ሁኔታ የጃማይካዊቷ ፀሀፊ ኤድዊጅ ዳንቲካትን "ሁሉም ስደተኞች አርቲስቶች ናቸው" የሚለውን አባባል ያስታውሳል። ፀሃፊዋ ይህንን የምትልበት ምክንያት አላት ይህም ስደተኞች ከስር መሰረታቸው ተነቅለው፣ ከዜሮ ጀምረው፣ አዲስ ህይወት መስርተው ቤትና አገርን በሚመስላቸው መልኩ ስለሚቀርፁት ነው።

ይህ ግን የኢትዮጵያውን ስደተኞች ብቻ እውነታ ሳይሆን የብዙ አገራት ስደተኞችም ጭምር ነው። የእነዚህ ስደተኞች ልጆችስ ኑሮ ምን ይመስላል፤ እስቲ በሌላው ዓለም እያንፀባረቁ ያሉ መኖሪያቸውን በምዕራቡ ዓለም ያደረጉ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሙዚቀኞችን ታሪክ በትንሹ እናጋራችሁ።

መክሊት ሐደሮ- ሁለገቧ ሙዚቀኛ

ከበሮው የሚደለቅበት፣ እልልታው የሚቀልጥበት፣ የደስታው ስሜት ሌሎችም ላይ የሚጋባበት የሠርግ ዘፈኖች በሕዝብ ዘፈንነታቸው ከትውልድ ትውልድ ቀጥለው የዘመንን አሻራ መወራረስን ያሳያሉ።

የባህል የሙዚቃ ዘፈኖች ባለቤትነታቸው የህዝብ እንደመሆኑ መጠን በተለያዩ ዘመናት የመጡ ሙዚቀኞችም የጊዜውን፣ የትውልዱን ድምፅ እየጨመሩ የዘመኑ ያደርጓቸዋል።

ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊቷ መክሊት ሐደሮም ሌላ ቀለም በመስጠት ታላላቆቹን ማይክል ጃክሰን እና አስቴር፣ ፕሪንስና ማህሙድ አህመድ፣ የጃዙን ፈጣሪ ኮልትሬን፣ ሜሪ አርምዴ፣ ሙላቱ አስታጥቄን በማንሳት ሁሉም በእሷ ማንነትና ሙዚቃ ውስጥ ቦታ እንዳለቸው በሙዚቃዋ ትናገራለች።

'አይ ዋንት ቱ ሲንግ ፎር ዜም ኦል' በሚለው ዘፈኗም የጣሉትን አሻራ በግጥሞቿ ውስጥ በማካተት በዜማው ለየት ያለ ተሰጥኦ ያለውን የሙሉቀን መለሰ አሻራንም አካታለች።

የሙዚቃ ቪዲዮውም እስክስታ፣ ኦሮምኛ፣ ጉራጊኛ፣ ትግርኛ ጭፈራ፤ ሂፕሆፕ ዳንስ፣ እልልታ፣ በአገር ልብስ ያሸበረቁ፣ አብስትራክት ስዕሎች፣ ስፌቶች ተካተውበታል፤ የመክሊት ማንነት መገለጫዎች።

መክሊት ሐደሮ ሁለገብ ሙዚቀኛ ናት። በሳንፍራሲስኮ፣ ካሊፎርኒያ መቀመጫዋን ያደረገችው መክሊት ከተለያዩ የሙዚቃ ስልቶች ሶውል፣ ጃዝ፣ ፎክና ኢትዮጵያ ሙዚቃ አይነትን ስልቶችም አቀላቅላ የአስቴርን ሙዚቃ "ዩ አር ማይ ላክ' በጉራጊኛና ጃዝ፣ ምን ሊመስል እንደሚችል፤ 'ከመከም' በጃዝ፣ የአርሶ አደሩ ህይወትን የሚነካውን አባይ ማዶን በጃዝ ቅላፄ ስትጫወተው ዘመንን ታሻግረዋለች፤ ሌላ ድምፅም ትሰጠዋለች።

መክሊት የተወለደችው ኢትዮጵያ ቢሆንም ቤተሰቦቿ ወደ አሜሪካ ያቀኑት በህፃንነቷ ነው፤ ያደገችውም አሜሪካ ነው። በያሌ ኮሌጅም ፖለቲካል ሳይንስ አጥንታለች። ከተመረቀችም በኋላ ወደ ሳንፍራንሲስኮ በመሄድ የከተማዋ የጥበብ ማዕከል ላይ ራሷን አገኘቸው። ወደ ሙዚቃው ዓለም የገባችው ዘግየት ብላ ነው።

በ24 ዓመቷ ወደ ሙዚቃ መምጣቷን በማስመልከት ራሷን 'ሌት ብሉመር' (ዘግይታ ያበበችው) ብላ ትጠራለች። ዘግየት ብላ ወደ ሙዚቃው ዓለም ለመግባት ምክንት የሆኗትም ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦቿ ናቸው። ከሙዚቃ በፊት ትምህርት ይቅደም በሚለው!

ምን አይነት መልዕክት ነው በሙዚቃ መተላለፍ ያለበት? ምናልባት ይሄንን ጥያቄ ናይጄሪያዊው ሙዚቀኛ ፌላ ኩቲ ቢጠየቅ 'አብዮትን ለማምጣት' ይላል።

ለመክሊት ግን ማንኛውም ነገር በሙዚቃ መተላለፍ ይችላል፤ ገደብ ሊኖረው አይገባም ትላለች። ሙዚቃ የህይወት ነፀብራቅ እንደ መሆኑ መጠን!

ሙዚቃ ማንኛውንም መልዕክት ሊያስተላልፍ ይገባል የሚል ጠንካራ እምነት አላት።

አንዳንድ ቀላል የሚመስሉ ሃሳቦች ደግሞ ትልቁን ፖለቲካዊ መዋቅር ያነቃንቁታል። ለምሳሌ የመክሊት ዘፈን ከመከምን ብንወስድ የኢትዮጵያ የፀጉር ስታይል ብቻ ከመሆን አልፎ በብራዚል፣በ ደቡብ አፍሪካና ሌሎችም የአፍሪካና የዓለም አገራት ውስጥ ያሉ ጥቁር ሴቶች ከተፈጥሮ ፀጉራቸው ጋር የሚያደርጉትን ትግል ይገልጻል።

ለዚያም ነው ከተለያዩ አገራት መክሊት ሙገሳንም፣ ውደሳንም የምታገኘው። በአንድ ወቅትም ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረገችው ቆይታ ከመከም ስላለው ተፅዕኖ ስትናገር "በሳንፍራንሲስኮ ቤይ አካባቢ የብላክ ላይቭ ማተርስ እንቅስቃሴ የሚያደራጁ ሴቶችን ባናገርኩበት ወቅት ከመከምን እንደ ብሔራዊ መዝሙር እንደሚያዩት ነገሩኝ። ሁልጊዜም ቢሯቸው ውስጥ እንደሚያጫወቱትና የሕዝባችን ማንነትና ፍቅርን የሚገልፅ ነው፤ ዘፈኑም ይህን እንዲያደርግ ነው የፈለግኩት፤ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ እንዲሁም ጥቁር ህዝቦች ጋር እንዲያገናኝ ነው ሐሳቤ" ብላለች።

ከባርነትና ቅኝ ግዛት ጋር ተያይዞ ሃብት መዝረፍ፣ አገራትን መቀራመትና ግድያ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ጥቁርነትን ሊወክል የሚችል ነገር ከቆዳ ቀለም ጀምሮ የፀጉር፣ የባህል ማንነት፣ ታሪክን የማስጠላት ሥራ ተሰርቷል፤ የነጭነትን የበላይነትንም ለማስረፅ በተሰራው ሥራ ብዙዎች ይሰቃያሉ።

በመላው ዓለም ቆዳን የማንጣት ሥራ በቢሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ዘርፍ ነው። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በነበረው የአፓርታይድ አገዛዝ የዘር ደረጃን ለማውጣት እርሳስን ፀጉር ውስጥ በማስገባት ፀጉሩ ከተዘናፈለ ነጭ፣ እርሳሱ እዛው ከቀረ ጥቁር እያሉ ለጭቆና ለመከፋፈል ተጠቅመውበታል።

ለዚያ ነው የመክሊት ሐደሮ "ከመከም" የተሰኘ ዘፈን ያንን ታሪካዊ ጭቆና፣ ማንነቱን የተቀማ ሕዝብ እንደገና የመመለስና ፖለቲካዊና የኃይል አሰላለፍን የሚነካ የሆነው።

መክሊት ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ቁርኝት ጠንካራ ነው። ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣው አባይ ማዶ በመጀመሪያ አልበሟ "ኦን ኤ ደይ ላይክ ዚስ" ውስጥ የተካተተው።

ምንም እንኳን ሌላ አገር ውስጥ ኑሯቸውን ያደረጉ ዲያስፖራ ሙዚቀኞች ወደ ኢትዮጵያ በየወቅቱ መመላለስ ባይችሉም አገራችን፣ መሰረታችን፣ መነሻችን የሚሏት ኢትዮጵያ፣ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ተፅእኖ ከፈጠረችባቸው ኢትዮጵያ ጋር የሚገናኙበትን ዘዴን ለመቀየስ አርባ ምንጭ ኮሌክቲቭ (የአርባ ምንጭ ስብስብ) የሚል ቡድንም መስራች ናት መክሊት።

ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያዊነትን ከቤተሰቦቻቸው ከተረዱት ሳይሆን በራሳችን መንገድ እንዴት ነው የምንረዳው በሚል 'ሆም አዌይ ፍሮም ሆም ' ከቤት ርቆ ቤት'- በሚል ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንን በጥበብ ያገናኘ ፕሮጀክትም ጀምረው ነበር።

መክሊት ሙዚቃ የተለያዩ ሕዝቦችን አንድ ላይ ያመጣል የሚል እምነት አላት። ለምሳሌ ለዓመታት የሰራችውን የናይል ፕሮጀክት ብንጠቅስ- በናይል ላይ ያለውን ፖለቲካ ወደጎን አድርገን በናይል ተፋሰስ ዙሪያ የሚኖሩ ሕዝቦችን ብናይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕዝቦች ይኖራሉ - የአባይን ፀጋ እየተቃመሱ።

እነዚህን ሕዝቦችስ አንድ ላይ በሙዚቃ ብናመጣቸው ምን ይመስላል? በአባይ የላይኛውና የታችኛው ተፋሰስ የሚኖሩ አገራትንም ሙዚቀኞች በማሰባሰብ በግብፅ፣ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እንዲሁም በአባይ አገራት ዙሪያ ዘፍነዋል፤ አንድነትን ሰብከዋል።

መክሊት "ዊ አር አላይቭ" የሚል ዘፈን አላት ምንም ቢሆን በህይወት መኖር ሐዘንም፣ ደስታም፣ የህይወት ትግል ውስጥ ብንሆን፤ በህይወት መኖር፣ ነገን ማየት ተስፋ ነው።

ከለላ ሚዛነ ክርስቶስ- የወደፊቱን የምታልመው

ከኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች በአሜሪካ የተወለደችው ከለላ ሚዛነ ክርስቶስ በሁለት ዓለማት ውስጥ መመላለስ ምን ይመስላል የሚለውን በሙዚቃዎቿ ውስጥ ታሳያለች። የማንነትን ብዙ ገጽታ በጥቁርነት፣ በሴትነት፣ የስደተኛ ልጅ በመሆን፣ በኢትዮጵያዊነት፣ በአፍሪካዊነት እንዲሁም በሌሎች የተደራረቡ ማንነቶች በሙዚቃዋ ውስጥ ይገለፃሉ።

'ሪትም ኤንድ ብሉዝ'፣ 'ሶውል'፣ ኤሌክትሮኒክ እንዲሁም ሌሎች ስልቶችን በማጣመር የራሷን ለየት ያለ የምትታወቅበትን ስልትም ማምጣት ችላለች።

"ሙዚቃዬ ካሉት ስልቶች ውስጥ አንዱ ነው እንዲባል አልፈልግም፤ ዋነኛው እቅዴ አዲስ መፍጠር ነው" ትላለች በአንድ ወቅት 'ለፒች ፎርክ' በሰጠችው ቃለ መጠይቅ።

እንዳው እድሉ ኖሯችሁ በከለላ ላይ የተፃፉ የተለያዩ ድረገፆችን ማየት ከቻላችሁ የሙዚቃ ጥልቀትን፣ መጠበብን እንዲሁም በሰው ልጅ የሚፈራረቁ ስሜቶች እናንተ እያለፋችሁበት እስኪመስል ድረስ ጎትቶ የማስገባት ኃይል አላት ይሏታል።

ሙዚቀኛ፣ የሙዚቃ ደራሲ የሆነችው ከለላ ስትፅፍ ዋናነት ከግምት ውስጥ የምታስገባው ጉዳይ ቢኖር " ከሁሉም ነገር በላይ ስለምን ማውራት ያስፈራኛል?" የሚለውን ነው።

ከዚያ በኋላም ሃሳቦቿን ሳትገድብ በነፃነት እንዲፈሱ ታደርጋቸዋለች፤ ከልቧ ጋር የምታደርጋቸውን ውይይቶች፣ ብዙዎች የግሌ ብለው የሚያስቡትን ታሪክ ከሰው ጋር ለመወያየት የሚያስፈሯቸውን ሃሳቦች፣ ለራሳቸው መድገም የማይፈልጉትን የልብ ስብራት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን ለማካፈል ወደኋላ አትልም።

በተለይም ከቀድሞ ጓደኛዋና ሙዚቀኛ (ቶሲን አባሲ) የነበራትን የፍቅር ግንኙነት ለአድማጮቿ "አንድ ሰው እየወደደሽም ሊጎዳሽ ይችላል፤ ብዙ ሰው ሊያልፍበት የሚችል ነገር እንደሆነ ይሰማኛል" በማለት አልበሟ ውስጥ አካታዋለች።

በሎስ አንጀለስ መቀመጫዋን ያደረገችው ከለላ በጎርጎሳውያኑ 1970ዎቹ ወደአሜሪካ ከተሰደዱት ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ነው የተደወለችው፤ ያደገችውም በሜሪላንድ ነው።

ለቤተሰቧ ብቸኛ ልጅ ናት፤ ከትምህርት ውጭ ያለውን አብዛኛውን ጊዜዋን ከአጎቶቿ ልጆች ጋር ታሳልፍ ነበር። መኪና ውስጥም ሆነው የትሬሲ ቻፕማንን ሙዚቃ ከፍ አድርገው ያጫውቱ ነበር፤ በተለይም "ፎር ዩ" የሚለው የትሬሲ ዘፈን ወደ ሙዚቃው ዓለም ከገባች በኋላ 'ከት ፎር ሚ' ለሚለው ዘፈን መነሻ ሆኗታል።

ከእሷ በፊትም ሆነ አሁን ላሉት ጥቁር አርቲስቶች ከፍተኛ ቦታ የምትሰጠው ከለላ ዊትኒ ሂውስተን፣ ጃኔት ጃክሰን ለሙዚቃዎቿ የጀርባ አጥንት ሆነዋታል። አባቷ ሚዛነ ክርስቶስ ዮሐንስ ይሰሟቸው የነበሩት ሚሪያ ማኬባ፣ ሃሪ ቤላፎንቴን፣ አስቴር አወቀ እንዲሁም ሌሎችም የሙዚቃውንም ሆነ የሌላውን ዓለም ዕይታዋን አስፍተውላታል።

በተለያዩ ማንነቶች ያደገችው ከለላ አስተዳደጓን እንዲህ ትገልፀዋለች፡

"እንደ አሜሪካዊ ሆኜ ነው ያደግኩት ቢሆንም ግን የመገለል ስሜት አለው፤ የሰረፀ ዘረኝነት አለ እንዲሁም ለብዙ ስደተኛ ቤተሰቦች ከውጭም ሆነ ከውስጥ የመሆን ስሜት አለው" ትላለች።

በአሜሪካ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የዘር ክፍፍል የተረዳቸውም ገና በታዳጊነቷ ነበር። ትምህርት ቤት ውስጥ በነበረ አቀማመጥ፤ ባትቀበለውም ሁሉም የመጣበትን አካባቢ መርጦ፣ ዘሩን ለይቶ ይቀመጥ ነበር።

የሙዚቃ ህይወቷም የጀመረው በህፃንነቷ ነው፤ ቫዮሊን ትጫወት ነበር፤ በትምህርት ቤቱ ባንድ ውስጥም ትጫወት ነበር። የሙዚቃ ህይወቷ በዚያው ቀጥሎ ዩኒቨርስቲም ከተቀላቀለች በኋላ በተለያዩ መድረኮች መዝፈን ጀመረች። ሙዚቃዋን በአንድ አይነት የማትወስነው ከለላ በአንድ ወቅት 'ዲዚ ስፔልስ' የተባለ ባንድም አባል ሆና ሜታል ሮክም ትጫወት ነበር።

ከለላ ሙሉ አልበሞች ባይሆኑም የተለያዩ ሙዚቃዎች ስብስቧን በጎርጎሳውያኑ 2013 'ከት ፎር ሚ' በሚል ርዕስ ፣ በ2015 እንዲሁ 'ሃሉሲኖንን' በሚል ያወጣች ሲሆን፣ የመጀመሪያ አልበሟ 'ቴክ ሚ አፓርት' የተለቀቀው ከሦስት ዓመታት በፊት ነው። አልበሟም ከመውጣቱ በፊት 'ፍሮንት ላይን'፣ 'ዌይቲን' እና 'ብሉ ላይት' የሚሉ ሙዚቃዎቿ የወጡ ሲሆን በከፍተኛ ሁኔታ አድናቆትንም አትርፋበታለች።

አልበሟም ከወጣ በኋላ ከፍተኛ ተሰሚነት አግኝቷል፤ በሙዚቃው ዘርፍ ባሉ ባለሙያዎችም ከፍተኛ ሙገሳን አግኝቷል። ከሁለት ዓመት በፊት በወጣው 'ከመሞታችሁ በፊት ልትሰሟቸው የሚገባችሁ 1001 አልበሞች' (1001 Albums You Must Hear Before You Die) መፅሀፍ ውስጥ የከለላ አልበም ተካቷል።

ገበያውን በማሰብ ሙዚቃ የማይሰሩ ተብለው ከሚነገርላቸው ሙዚቀኞች መካከል አንዷ የሆነቸው ከለላ ሶላንጅን ከመሳሰሉ ዘፋኞችም ጋር ተጣምራለች።