በሮማኒያ የጣፊያ ካንሰር ህሙሟ በቀዶ ሕክምና ላይ እያለች በደረሰባት ቃጠሎ መሞቷ ተሰማ

የቀዶ ጥገና ባለሙያዎች በቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሮማኒያ በቀዶ ሕክምና ወቅት በተፈጠረ እሳት የካንሰር ሕሙሟ ሕይወቱ ማለፉ ተሰማ።

ሮማኒያ ቡቻሬስት በሚገኘው በፍሎሬስካ ሆስፒታል የጣፊያ ካንሰር ለመታከም ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል የገባችው ታካሚ የተደረገላት አልኮልነት ያለው ፀረ ተባይ ከእሳት ጋር በመያያዙ ለሕይወቷ መጥፋት ምክንያት ሆኗል ተብሏል።

የቀዶ ሕክምናውን ለማካሄድ የተጠቀሙት ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌትሪክ ቀዶ ሕክምና መሳሪያ የፈጠረው ሙቀት ከአልኮሉ ጋር ስለተገናኘ ታካሚዋ በቀዶ ሕክምና አልጋ ላይ ባለችበት መላ አካሏ በእሳት ተያይዟል።

በእሳቱ ከባድ ቃጠሎ የደረሰባት ሲሆን በሆስፒታሉ ለሳምንት ያህል ሕክምና ስታገኝ ቆይታ ሕይወቷ አልፏል።

የሟች ቤተሰቦች ለሮማኒያ መገናኛ ብዙኀን እንደተናገሩት በወቅቱ " የጉዳቷ መጠን " ወይንም ምን እንደተፈጠረ አልተነገራቸውም ነበር፤ እንዲሁ "አደጋ አጋጥሟታል" መባላቸውን ገልጸዋል።

"የተፈጠረውን ነገር በቴሌቪዥን ላይ ሲተላለፍ ነው የሰማነው" በማለት "ማንንም ለመውቀስና የማንንም ስም ለማጥፋት ሳይሆን በትክክል ምን እንደተፈጠረ ማወቅ እንፈልጋለን" ብለዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ቪክቶር ቾስታቼ ይህንን "ዘግናኝ" ክስተት ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ምን እንደተፈጠረ ይፋ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

በመግለጫቸው ላይ "ከዚህ አስደንጋጭ ክስተት ለመማር እንሞክራለን" ያሉ ሲሆን " እኔም ሆንኩ የማስተባብረው ቡድን ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ የየበኩላችንን እናደርጋለን" ብለዋል።

ምክትል ሚኒስትሩ ሆራቲዩ በበኩላቸው "የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎቹ የኤሌትሪክ ቀዶ ሕክምና መሳሪያ በሚጠቀሙበት ወቅት አልኮልነት ያለው ፀረ ተባይ መጠቀም የተከለከለ መሆኑን ማወቅ ነበረባቸው" ብለዋል።

ሮማኒያ ከአውሮፓ አባል ሀገራት በአጠቃላይ ዝቅተኛ የሆነ የሕክምና አሰጣጥ ያለባት ሀገር ስትሆን፣ የጤና ተቋማቷ በአግባቡ ያልተሟሉ፣ ጤና ባለሙያዎች እጥረት ያለባት ሀገር ናት።