#7 እሷ ማናት፡ ከሊስትሮነት እስከ ከተማ አውቶቡስ አሽከርካሪነት

ትዕግሥት ደሳለኝ እባላለሁ። ውልደቴና እድገቴ ባህር ዳር ሲሆን የከተማ አውቶቡስ ሹፌር ነኝ። ቤተሰቦቼ አቅማቸው ዝቅ ያለ ስለነበር የራሴን ኑሮ ለማሸነፍ ያልሰራሁት ሥራ የለም።

ራሴን ለመለወጥ ጫማ ጠርጌያለሁ፣ የታክሲ ረዳትም ነበርኩ፣ ከወንድ እኩዮቼ ጋር የተገኘውን ለመስራት ተጋፍቼያለሁ።

ከልጅነቴ ጀምሮ ወንዶች የሚሰሩትን ሥራ ሁሉ እሰራ ነበር። ትምህርቴን ከዘጠነኛ ክፍል አቋርጬ ነበር የታክሲ ረዳት የሆንኩት። የታክሲ ረዳትነትን ለሦስት ዓመት ያህል ሰርቻለሁ።

ከታክሲ ረዳትነት በማገኘው ገንዘብ ቤተሰቦቼን ማገዝ ብሎም ማስተዳደር ከመቻሌ በላይ እህቴ ትምህርቷን እንድትከታተል ማድረግ ችያለሁ።

ባህር ዳር እኔ የታክሲ ረዳት በነበርኩበት ወቅት እኩዮቼ የነበሩ ሴቶች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ለመናገር የሚፈሩበት፣ ከቤት ለመውጣት የማይደፍሩበት ስለነበር የታክሲ ረዳትነት ሥራ ላይ መሰማራቴ በሰዉ ዘንድ እንደ ትንግርት የሚታይ ነገር ነበር።

ለእኔ ግን የእለት ጉርስ ማሸነፊያ፣ የእናቴን ማጀት የምሞላበት፣ እህቴን ትምህርት ቤት የምልክበት የሥራ መስክ ሆኖልኝ ነበር።

የምሰራውን ለማሻሻል ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ የታክሲ ረዳትነት እየሰራሁ ሦስተኛ መንጃ ፈቃድ አወጣሁ። በዚህም ታክሲ ረዳት እያለሁ መንጃ ፈቃዴን ላወጣ እንደሆነ የሚያውቁ ሰዎች ቃል ይገቡልኝ እንደነበር አስታውሳለው።

"አንቺ መንጃ ፈቃድሽን ጨርሺ እንጂ የሥራ ነገር አያሳስብሽ" የሚሉኝ በርካታ ሰዎች ነበሩ። መንጃ ፈቃዴን ጨርሼ ስነግራቸው ግን ቃላቸውን አጠፉ።

መንጃ ፈቃዴን አሳይቼ ሥራ የጠየቅኋቸውም ሰዎች ደፍረው መኪናቸውን ሊሰጡኝ አልፈለጉም። ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ሴት መሆኔ በእኔ ላይ እምነት እንዳይጥሉ ስላደረጋቸው ነበር።

ከዚያም ሊስትሮነት መስራት ጀመርኩ። ሊስትሮነት እየሰራሁ አንድ የኮንስትራክሽን ድርጅት የቀን ሰራተኛ እንደሚፈልግ የሚገልጽ ማስታወቂያ ለጥፎ ሳይ ሄጄ ተቀጠርኩ።

የኮንስትራክሽን እቃዎችን እየተሸከሙ የግንባታውን ሥራ ማቀላጠፍ ለእኔ ከባድ አልሆነም። ከወንድ ጋር ተጋፍቼ፣ የሴት የወንድ ሥራ ሳልል ስሰራ ስላደግሁ ለእኔ ይህ ከባድ አልነበረም።

ከእዚያ በኋላም የቀን ሥራ እሰራበት የነበረው ድርጅት አሽከርካሪ እንደሚፈልግ ማስታወቂያ ሲወጣ ተወዳድሬ ቦታውን ለማግኘት ቻልኩ። ከዚያም የሹፍርና ሥራዬን ተቀጥሬ እየሰራሁ አራተኛ መንጃ ፈቃዴን አወጣሁ።

ትልቁ መሰናክል - በራስ መተማመን አለመኖር

በዙሪያዬ ያሉ በርካታ ሴቶችን ስመለከት ከሕይወት ስኬትና ከግባቸው ሳይደርሱ የሚያስቀራቸው ነገር በራስ መተማመን ስለሚያንሳቸው ነው። ውጤታማ እንዳይሆኑ፣ የሕይወት ጥሪያቸውን እንዳይከተሉ፣ በቤት ውስጥ እንዲቀሩ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ቀዳሚው በራስ መተማመን አለመኖር መሆኑ ይገባኛል።

ሴት መሆን ብቻውን የሚያጎለው ነገር የለም። ከማንኛውም ሰው እኩል፣ ከማንኛውም ወንድ ጋር በአቻነት ወጥተን መግባት፣ ሰርተን ማደርና ራሳችንንም ሆነ ቤተሰቦቻችንን ማስተዳደር እንችላለን።

ባለትዳርና የአምስት ልጆች እናት ነኝ። መደበኛ ሥራዬን ብቻ ሳይሆን በቤት ውስጥ የእናትነት ድርሻዬንም እወጣለሁ። ማለዳ ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ልጆቼን ምሳ ማብሰልና መቋጠር ይጠበቅብኛል። ከሥራ ስገባም የተለመደው የቤት ውስጥ ሥራ የእኔ ድርሻ ነው።

ምሳ ሰዓት ወደ ቤት ስገባም ቢሆን የቤት ውስጥ ሥራ እኔኑ ነው የሚጠብቀው። ተደራራቢ የሆነ ኃላፊነት ቢሆንም እጥራለሁ። የቤተሰቤን፣ የማህበራዊ ህይወቴን እንዲሁም የግል ህይወቴን ለማጣጣም እሞክራለሁ።

ከተወለድኩባት ከተማ ወጥቼ የተለያየ አካባቢ ተንቀሳቅሼ ሰርቻለሁ። ሴት መሆኔ በሕይወት ስኬት ብቻ ሳይሆን ከስፍራ ስፍራ ተንቀሳቅሼ እንዳልሰራ አላደረገኝም። ጣና በለስ፣ ግቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታ ላይ ሰርቼያለሁ።

በዱር ቤቴ ወደ ሱዳን የሚያገናኝ የመንገድ ሥራ ላይ ተሳትፌያለሁ። በእነዚህ ስፍራዎች ላይ ገልባጭና ፒክ አፕ መኪኖችን እየሾፈርኩ ነበር የምሰራው። የከተማ አውቶቡስ ደግሞ ሐዋሳ ውስጥ ለአራት ዓመት፣ አዳማ ውስጥ ደግሞ ለአንድ ዓመት አሸከርክሬያለሁ።

ብዙ ሰው በሥራዬ ያበረታታኛል፤ ያደንቀኛል። እኔን አይተው መንጃ ፈቃድ ማውጣት የሚፈልጉና መንጃ ፈቃድ የማውጣት ሂደትን የጀመሩ ሴቶች አሉ።

በአሁኑ ሰዓት አብረውኝ የሚሰሩ ትኬት ቆራጮችን ራሳቸውን እንዲለወጡ እመክራለሁ። በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ ሴት አሽከርካሪዎች ቢበዙ ለመንገድም ሆነ ለተሳፋሪ ደህንነት መልካም እንደሆነ ይሰማኛል።

ለምሳሌ እኔ ጥፋት ሰርቼ ተከስሼ አላውቅም፤ ተጋጭቼም አላውቅም። ሴቶች ስናሽከረክር ጥንቁቆች መሆናችን ይታወቃል።

ወደፊት አቅሜ ጠንከር ሲል በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶችን በማሰባሰብ እና ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራ ማሰማራት ብችል ደስ ይለኛል።