ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጎርፍ ባጠቃቸው የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ተጨማሪ ዝናብ ሊጥል ይችላል ተባለ
ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ ከባድ የጎርፍ አደጋ ባጋጠማት ሶማሊያ በቀጣይ ቀናትም ተጨማሪ ዝናብ ሊጥል እንደሚችል የአየር ሁኔታ ትንበያ ሙያተኞች ገለጹ።
በጎርፉ ሳቢያ ወደ 273,000 የሚጠጉ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንደሸሹ 'ኢንተርናሽናል ሬስኪው ኮሚቴ' የገለጸ ሲሆን፤ 'አክሽን አጌንስት ሀንገር' የተባለው ድርጅት ደግሞ የጎርፍ አደጋው ከዚህ ቀደም ከደረሱት እጅግ የከፋ ነው ብሏል።
በጎርፉ የኬንያ እና የደቡብ ሱዳን አንዳንድ ቦታዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ደቡብ ሱዳን ውስጥ ከ600,000 የሚበልጡ ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል። ባለፈው ረቡዕ ፕሬዘዳንት ሳልቫ ኪር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸውም የሚታወስ ነው።
ፒቦር የተባለችው የአገሪቱ ግዛት ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ገልጸዋል። "ከተማዋ ሙሉ በሙሉ በውሀ ተውጣለች። ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል" ሲሉ 'ሜዲካል ሳን ፍሮንቴይርስ' የተባለው የደቡብ ሱዳን የአደጋ ጊዜ አስተባባሪ ወኪል ኢድ ፈርዲናንድ አቴ ተናግረዋል።
በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ኮሚቴ ኃላፊ አንድርያ ኖይስ እንዳሉት፤ በጎ አድራጊዎች ሰዎችን ለመርዳት በጎርፍ የተሞሉ ጎዳናዎች ማለፍ ይጠበቅባቸዋል።
"ሰዎችን የምንረዳው እስከ ጉልበታችን እና ታፋችን የሚደርሰውን ውሀ አልፈን ነው"ሲሉ ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል።
በጎርፍ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች መቼ፣ ምን ያህል ዝናብ ሊጥል እንደሚችል አስተማማኝ መረጃ የለም። ሆኖም ኬንያ ውስጥ ጥቅምት ወር ላይ ኃይለኛ ዝናብ እንደጣለ ታውቋል።
በኬንያዋ ሞምባሳ ጥቅምት 16 ላይ 100 ሚሊ ሜትር ዝናብ ጥሏል። ይህም በወሩ ከተመዘገበው የዝናብ መጠን የላቀ ነው።
ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የዝናብ መጠን ለመጨመሩ ምክንያቱ 'ፖዘቲቭ ኢንድያን ኦሽን ዲፖል' በመባል የሚታወቀው የአየር ሁኔታ ነው። ይህ የሚፈጠረው ምዕራባዊው የህንድ ውቅያኖስ ከምሥራቃዊው ክንፍ በላይ ሲሞቅ ነው።
ዛሬና ነገ እንዲሁም በቀጣዩ ሳምንት ጭምር በሶማሊያ ከፍተኛ ዝናብ እንደሚጥል ይጠበቃል።