የትራምፕ የስልክ ጥሪ ሲተነተን

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር ያደረጉት የስልክ ልውውጥ ይፋ ሆኗል። ዲሞክራቶች ዛሬም እርሳቸውን ከስሶ ተጠያቂ ለማድረግ ደፋ ቀና እያሉ ነው። ይፋ ከሆነው የስልክ ጥሪ ምን ነገሮች ጎልተው ወጡ?

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የዩክሬኑ አቻቸው ዜሌንስኪ በወርሃ ሐምሌ ያደረጉት የስልክ ልውውጥ በተቺዎቻቸው እንዲብጠለጠሉ አድርጓቸዋል። የምርጫ 2020 ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደንን ጥላሸት ለመቀባት የውጪ ኃይል እርዳታ ጠይቀዋል ሲሉም ይከስሷቸዋል።

ከስልክ ምልልሶቹ ውስጥ ጎልተው የወጡት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።

1. ጆ ባይደን ስቴ ተጠቅሰዋል

ትራምፕ በስልክ ልውውጡ ወቅት "ስለ ባይደን ልጅ በርካታ የምንነጋገረው ነገር አለ። ባይደን ልጁ እንዳይጠየቅ አቃቤ ሕጉ ማድረጉን በርካቶች ማወቅ ይፈልጋሉ። ስለዚህ ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጋር ማንኛውንም ነገር ብታደርግና ጉዳዩ ቢታይ መልካም ነው። ባይደን ልጁን ከተጣያቂነት ስለማስመለጡ በአደባባይ ጉራውን ይቸረችራል፤ ስለዚህ ጉዳዩን ብታየው. . . ለኔ መቼም እንዲህ አይነት ነገር ዘግናኝ ነው" ብለዋል።

ይህ ትራምፕ ዩክሬን የባይደንን ጉዳይ እንድትመለከተው እየተጫኗት መሆኑን ያሳያል ይላሉ ተንታኞች።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለዩክሬኑ ፕሬዝዳንት የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ሕግን ጄነራል ቢል ባርን እንዲያናግሯቸው ነግረዋቸዋል። ነገር ግን የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ በዚህ ጉዳይ እጃቸውን እንዳላስገቡ ጠቅሷል።

2. የትራምፕ እከክልኝ ልከክልህ ጥያቄ

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ "በመከላከያ ረገድ እያደረጉት ስላለው ድጋፍ ላመሰግን እወዳለሁ። በቀጣዮቹ እርምጃዎች ላይ ለመተባበር ዝግጁ ነን። ለመከላከያ ኃይላችን ተጨማሪ ፀረ ታንክ ለመግዛት ዝግጁ ነን" ብለዋል።

ትራምፕ በምላሹም "አንድ ውለታ እንድትውልልኝ ልጠይቅህ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም አገራችን በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ማለፏን ዩክሬንን መቼም አይጠፋትም" ብለዋል።

በዚህ የስልክ ምልልስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በግልፅ የሌላ አገር ፕሬዝዳንትን ውለታ ጠይቀዋል ይላሉ ተንታኞች። ነገር ግን በምላሹ ምን እንደሚሰጡ ግልፅ አይደለም በማለትም ከዚህ የስልክ ምልልስ ቀደም ብሎ የተከናወነ ድርጊትን ያጣቅሳሉ።

ከዚህ የስልክ ምልልስ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ትራምፕ ኮንግረስ ለዩክሬን ያፀደቀውን የ250 ሚሊየን ዶላር የወታደራዊ እርዳታ እስከ መስከረም አጋማሽ በሚል አዘግይተውት ነበር። ለዚህም ግልፅ ማብራሪያ በወቅቱ አለመቅረቡ ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እያለ ነው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ከአሜሪካ ፀረ ታንክ ለመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው የገለፁት። ፕሬዝዳንቱ ይህንን ንግግራቸውን እንደጨረሱ ትራምፕ "ውለታ" ያሉትን ጠየቁ፤ ከዚህ በኋላ ነው የጆ ባይደን ስም የተነሳው።

ዲሞክራቶች፤ ይህ የስልክ ቃለ ምልልስ ይፋ ከመሆኑ በፊት ትራምፕ የያዙትን የዩክሬን ወታደራዊ እርዳታ፤ ዩክሬን ዋነኛ የምርጫ ተቀናቃኛቸው ላይ ምርመራ ከጀመረች ለመልቀቅ ጠይቀዋል ሲሉ ወንጅለዋቸው ነበር።

ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ግልፅ ያለ ጥያቄ ሲያቀርቡ የሚያሳይ የስልክ ምልልስ አልተገኘም። ዲሞክራቶች ግን ቢሆንም እዚህና እዚያ ያሉ ነጥቦችን አገናኝቶ የነገሩን ዳር ዳርታ ማወቅ ቀላል ነው ሲሉ ይናገራሉ።

3. አውሮፓውያንን ድምፃቸው ሊሰማ ይገባል

ትራምፕ በዚህ የስልክ ምልልሳቸው ወቅት "ለዩክሬን በርካታ ነገር አድርገናል። የአውሮፓ አገራት ከሚያደርጉት በላይ በርካታ ጉልበትና ጊዜ አፍስሰናል። ድጋፍ ሊያደርጉላችሁ ይገባል። ጀርመን ምንም ነገር አላደረገችላችሁም። ያደረጉት ነገር ቢኖር ወሬ ብቻ ነው። እኔ እንደሚመስለኝ ልትጠይቋቸው ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል።

ሪፐብሊካን ከዚህ ንግግር ተነስተው ትራምፕ ወታደራዊ እርዳታውን የያዙት ለዚህ ነው እያሉ ነው። ይህ ደግሞ ለትራምፕ ጥሩ መከላከያ ሆኗል።

ከዚህ በፊት ፕሬዝዳንት ትራምፕ እርዳታው ለምን እንደዘገየ ሲናገሩ ከዚህ ቀደም በሶቪየት አገራት ያለውን ሙስና አንስተው ነበር። ከማክሰኞ እለት ወዲህ ግን ይህንን ነጥባቸውን ትተው አሜሪካ ለዩክሬን በርካታ ድጋፍ በማድረጓ የአውሮፓ አገራት ላይ ግፊት ለማሳደር ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

በጉዳዩ ላይ ዲሞክራቶችና ሪፐብሊካን ቢከራከሩበትም ፍርዱን ግን የሚሰጠው የአሜሪካ ሕዝብ ይሆናል።

4. ትራምፕ በአቅም ማነስ የተባረረን የዩክሬን አቃቤ ሕግ ጋፈዋል

"ጎበዝ የሆነ አቃቤ ሕግ እንዳለህ ሰምቻለሁ፤ መታገዱ አግባብ አይመስለኝም። በርካታ ሰዎች ይህ ጎበዝ አቃቤ ሕግ ከሥራው የታገደበት ምክንያት አግባብ አለመሆኑንና አንዳንድ መጥፎ ሰዎች ከእርሱ መታገድ ጀርባ እንዳሉ እያወሩ ነው። ሚስተር ጊዩላኒ በጣም የተከነበረ ሰው ነው። የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ነው። እንዲደውልልህ አደርጋለሁ። ከጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ጋር ሆኖ እንዲደውልልህ አደርጋለሁ"

ይህ ትራምፕ የጠቀሱት የዩክሬን አቃቤ ሕግ ከሥራው የተሰናበተው ብቁ አይደለም ተብሎ ነው። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን በአግባቡ እንዳልተስተናገደ ጠቅሰዋል።

አቃቤ ሕጉ ቪክቶር ሾኪን የሚባል ሲሆን በዩክሬን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከስራው የተባረረው በ2016 ነበር።

ጆ ባይደን እና ሌሎች የአሜሪካ ባለስልጣናት፤ የአውሮፓ አጋሮቻቸው እና የዩክሬን የለውጥ ኃይሎች የሚባሉት ግለሰቡን ሙሰኛ ነው ሲሉ ይገልፁታል።

እዚህ ላይ ስማቸው የተጠቀሰው የቀድሞ የኒውዮርኩ ከንቲባ የትራምፕ የግል ጠበቃ ናቸው። ጠበቃው የፕሬዝዳንቱን የዩክሬን ጉዳይ እንዲይዙላቸው መጠቀሳቸው መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ነው።