የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ በዘረኛ ፎቶግራፋቸው እየተተቹ ነው

ከሁለት አሠርት ዓመታት በፊት በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ በተካሄደ ድግስ ላይ፤ የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ ፊታቸውን ቡናማ ቀለም ተቀብተው የሚያሳይ ፎቶግራፍ በ 'ታይም' መጽሔት ይፋ ተደርጓል።

ፎቶው ይፋ ከተደገ በኋላ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ "ባደረግኩት ነገር እጅጉን ተጸጽቻለሁ፤ የተሻልኩ ሰው ሁኜ መገኘት ነበረብኝ" ብለዋል።

ድግሱ የተከናወነው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2001 ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ያስተምሩበት በነበረ አንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር። ጀስቲን ቆዳ የሚያጠቁር 'ሜክ-አፕ' (መዋቢያ) ፊታቸውን እንዲሁም እጃቸውንም ተቀብተውም ነበር።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ፒየሬ ትሮዶ ልጅ የሆኑት ጀስቲን ትሩዶ፤ የፊታችን ጥቅምት ላይ የምርጫ ውድድር ይጠብቃቸዋል።

'ታይም' የጠቅላይ ሚንትሩን ፎቶ የያዘ ዘገባ ካስነበበ በኋላ፤ ድርጊታቸው ዘረኛ እንደነበረ አምነው "ማድረግ አልነበረብኝም" ብለዋል። 'አረቢያን ናይትስ' በሚል የተሰየመው ድግስ ላይ አላዲን የተባለውን ገጸ ባህሪ ተላብሰው እንደተገኙም ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

ጋዜጠኞች፤ ጠቅላይ ሚንስሩ ከ2001ዱ ድግስ በፊት ወይም በኋላ ፊታቸውን ቡናማ ቀለም ተቀብተው እንደሆነ ጠይቀዋቸው ነበር።

"የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ በተደረገ የተሰጥኦ ውድድር ላይ ቡናማ ቀለም ተቀብቼ ነበር" ብለው ምላሽ ሰጥተዋል።

'ናሽናል ካውንስል ኦፍ ክኔዲያን ሙስሊምስ' የተባለው የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ማኅበር የጠቅላይ ሚንስትሩን ድርጊት ኮንነዋል።

የማኅበሩ ዋና ኃላፊ ሙስጠፋ ፋሩቅ "ጠቅላይ ሚንስትሩ ቡናማ ወይም ጥቁር ቀለም ተቀብተው ማየት እጅግ ያሳዝናል። የምሥራቁ ዓለም በተዛባ መንገድ ወደሚሳልበት ዘረኛ ዘመን የሚወስድም ነው" ብለዋል።

የተቀናቃኝ ፓርቲ መሪ የሆኑት አንድሪው ሺር፤ "ፎቶው በ2001 ዘረኛ እንደነበረው ሁሉ አሁን ባለንበት ዘመንም ዘረኛ ነው፤ አገሪቱን ለመምራት ብቁ አይደሉም" ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትሩን ወቅሰዋል።

'ኒው ዴሞክራቲክ ፓርቲ' የተባለው ፓርቲ መሪና የሲክ ሀይማኖት ተከታይ የሆኑት ጃግመንት ሲንግህ "ፎቶው ክብረ ነክ ነው" ብለዋል።

ጃግመንት ሲንግህ ቶሮንቶ ውስጥ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ሳለ "አንድ ሰው ቡናማ ወይም ጥቁር ቀለም ሲቀባ በጥቁሮች ላይ እየተሳለቀ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የ 'ግሪን ፓርቲዋ' ኤልዛቤጥ ሜይም ጠቅላይ ሚንስትሩን ተችተዋል።

ይህ ፎቶግራፍ ተራማጅ ፖሊሲዎች አሉኝ የሚሉት ጀስቲን ትሩዶን ገጽታ የሚያጠለሽ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ ጠቅላይ ሚንስትር ሆኖ ለመመረጥ እየተወዳደሩ ያሉት ጀስቲን፤ በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ያጡ ይሆን? የሚል ጥያቄም አጭሯል።