ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ድሬ ዳዋ ስለሚገኙት የለገ ኦዳ የዋሻ ሥዕሎች ያውቃሉ?
ከድሬ ዳዋ ከተማ 36 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የለገ ኦዳ ዋሻ ወደ 600 የሚጠጉ ጥንታዊ የዋሻ ሥዕሎች ይገኙበታል። በ1920ዎቹ አካባቢ በተመራማሪዎች ዕውቅና እንዳገኙ የሚነገርላቸው የዋሻ ሥዕሎች ከ7,000 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠሩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በብዛት በቀይ፣ በቢጫና ግራጫ ቀለም ከተሠሩት ሥዕሎች መካከል የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳ ቁሶች እንዲሁም እንስሳት የሚያሳዩት ይገኙበታል።
የድሬ ዳዋ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ባለሙያ የሆኑት አቶ ደረጄ ታደሰ፤ ሥዕሎቹ ጥንት በአካባቢው ይኖሩ በነበሩ ሰዎች እንደተሠሩና፤ የአኗኗር ዘይቤያቸውን እንደሚያሳዩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሥዕሎቹ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋም እንደተጋረጠባቸው አቶ ደረጄ ተናግረዋል። ዋሻ ሥር የሚገኙት ሥዕሎች በዝናብ ሳቢያ እየደበዘዙ መጥተዋል። በሰው ንክኪ ምክንያትም የቀድሞ ይዘታቸውን እያጡ ነው።
አቶ ደረጄ እንደሚሉት፤ ቅርሱ በአግባቡ ባለመያዙ የአገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል።
ቅርሱን ከዝናብ ለመከላከል መጠለያ ቢሠራም፤ የበለጠ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ባለሙያው ተናግረዋል። የቢቢሲ ባልደረባ ወደሥፍራው አቅንቶ ካነሳቸው ፎቶግራፎች የሚከተሉት ይገኙበታል።