ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት የምግብ ምርት ከውጪ እንዳይገባ አዘዙ
የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሃማዱ ቡሐሪ የሃገር ውስጥ የእርሻ ምርትን ለማሳደግ ሲሉ ማዕከላዊው ባንክ የምግብ ምርቶችን ከውጭ ለሚያስገቡ አስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ እንዳይሰጥ አዘዙ።
ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት የሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ኢኮኖሚውን ለማስፋፋት በሚጠቅም መንገድ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል እንጂ "ጥገኝነትን በሚያበረታቱ ከውጭ የሚመጡ ምግቦችን ለመግዛት በሚደረግ ወጪ ላይ መዋል የለበትም" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ "ወደ ናይጄሪያ ምግብ ለሚያስመጣ ማንኛውም ሰው ሰባራ ሳንቲም አንሰጥም" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ናይጄሪያ በአፍሪካ ውስጥ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ስትሆን፤ 200 ሚሊዮን የሚጠጋውን ሕዝቧን ለመመገብም በአብዛኛው የምግብ ምርቶችን ከውጭ ታስገባለች።
በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ በተካሄደው ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ ያሸነፉት ቡሐሪ፤ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው የተዳከመውን የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሻሻል ቃል ገብተው ነበር።
ናይጄሪያ በአፍሪካ ውስጥ ትልቋ የነዳጅ ዘይት አምራጭ ስትሆን ከምርቱ የምታገኘው ገቢና ግብር ለኢኮኖሚዋ ወሳኝ ሲሆን አብዛኛው ገቢም ከውጭ ምግብ፣ መሰረታዊ ቁሳቁሶችና ከባድ ማሽኖች ለማስገባት ታውለዋለች።
በሃገሪቱ ብሔራዊ ስታትስቲክስ ጽህፈት ቤት መረጃ መሰረት ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት ውስጥ ናይጄሪያ የግብርና ምርቶችን ለመግዛት 503 ሚሊዮን ዶላር አውጥታለች። ይህ አሃዝም ባለንበት የፈረንጆች ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ላይ ከ25 በመቶ በላይ ጨምሯል።
ፕሬዝዳንቱ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ወቅት የሃገሪቱ ሕዝብ ዋነኛ ምግብ የሆነውና በበርካታ ግዛቶቿ የሚመረተውን ሩዝ ለማስገባት የውጪ ምንዛሪ እንዳይሰጥ አግደዋል።
ይህ እርምጃ ዓላማ ያደረገው የሃገር ውስጥ ምርትን ማበረታታት ቢሆንም በተቃራኒው በአብዛኛው ከጎረቤት ቤኒን ከፍተኛ መጠን ያለው ሩዝ በድብቅ በድንበር በኩል እንዲገባ ምክንያት ሆኗል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ማዕከላዊው ባንክ ናይጄሪያ ውስጥ የሚመረተውን ወተት ለማበረታታት በማለት የወተት አስመጪዎች የውጪ ምንዛሪ እንዳይሰጣቸው ከልክሏል።
የሃገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ከመንግሥት ተጽዕኖ ነጻ በመሆኑ ራሱ ከሚወስደው ርምጃ ውጪ የፕሬዝዳንቱን ትዕዛዝ እንዴት እንደሚያስተናግደው እስካሁን ግለጽ አይደለም።
ውሳኔው ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ አስመጪዎች የውጪ ምንዛሬ በከፍተኛ ዋጋ ከሚሸጥበት ጥቁር ገበያን ከመሳሰሉ አማራጮች የውጪ ምንዛሪ ስለሚገዙ በምግብ ዋጋ ላይ ጭማሪ መከሰቱ አይቀርም ተብሏል።