ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤላዊው ቢሊየነርና ረዳቶቹ ለጊኒ ባለስልጣናት ሙስና በመስጠት ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው
እስራኤላዊው ቢሊየነር ቤኒ ስቴይንሜትዝ እና ሁለት ረዳቶቹ በጊኒ የማእድን ማውጣት ፍቃድ ለማግኘት ለባለስልጣናቶቹ ጉቦ በመስጠት ተከስሰው ችሎት ፊት ሊቀርቡ መሆኑን የስዊዝ አቃቤ ሕግ አስታወቀ።
ሶስቱ ተጠርጣሪዎች 10 ሚሊየን ዶላር ለቀድሞ የጊኒ ፕሬዝዳንት ላንሳና ኮንቴ ሚስት መክፈላቸው ተገልጿል።
ስቴይንሜትዝ እና የማእድን አምራች ኩባንያቸው እንዲህ አይነት ነገር አይነካካንም ሲሉ ክሱን አስተባብለው ነበር።
አቃቤ ሕግ ሁለቱ ተከሳሾች በአስር ዓመት እስር እንዲቀጡለት ይፈልጋል።
ከስድስት ዓመት በፊት አቃቤ ሕግ ስቴይንሜትዝ በጊኒ ደቡብ ምስራቅ በምትገኘው ሲማንዳኡ ክልል ለሚገኘው ሲማንዳኡ ማእድን ማምረቻ ፈቃድ ያገኘው ሙስና በመስጠት ነው ሲል ነበር ምርመራውን የጀመረው።
ገንዘቡ በከፊል ለጊኒ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሚስት በስዊዝ በሚገኝ ባንክ በኩል ገቢ መደረጉ ተገልጿል።
በዚህ አመት የካቲት ወር ላይ የጊኒ መንግስት በስቴይንሜትዝ እና ቢኤስጂአር ላይ ከፍተውት የነበረውን የሙስና ክስ በመተው በምላሹ በሲማንዳኡ ማእድን ማውጫ ላይ ያላቸውን መብት አግኝተዋል።
የጊኒ መንግስት በስዊስ ምርመራ ላይ አለመሳተፉን ገልጾ ከቢኤስጂአር ጋር "አላስፈላጊ ውዝግብ" ውስጥ መግባት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።
በ2016 ስቴይንሜትዝ ከማእድን ማውጣት ስራቸው ጋር በተያያዘ በእስራኤል መንግሥት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ የተደረገባቸው ሲሆን በወቅቱ ምንም አይነት ጥፋት አለመስራታቸውን ተናግረው ነበር።
ሲማንዳኡ በአለማችን ከፍተኛ የሆነ የብረት ማእድን ክምችት የሚገኝበት ስፍራ ነው።
ጊኒ በማእድን ኃብት ከበለፀጉ የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን ዜጎቿ ግን በቀን ከ27 ብር በታች ገቢ የሚያገኙ ምንዱባን ናቸው።