ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አስራ አምስት ወጣቶችን ያጣችው ኢሮብ ወረዳ
ብዙዎች የተሻለ ህይወትን ፍለጋ፣ በረሃ አቋርጠው፣ ወንዙን ተሻግረው፤ ለሰው ልጅ አእምሮ ከባድ የሚመስሉ ውጣ ውረዶችን አልፈው ነገን ተስፋ አድርገው ይጓዛሉ።
ለዓመታትም ብዙ ኢትዮጵያዊያን ረሃብ ሳይበግራቸው፤ ቁር ሳይፈትናቸው በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ የሚያደርጉት ጉዞ አሁንም በአደገኛ ሁኔታ እንደቀጠለ ነው።
በቅርብ ጊዜያትም ይህን ያህል ኢትዮጵያዊያን በቀይ ባህር ሰምጠው ሞቱ፤ ድንበር ሊያቋርጡ ሲሉ ተያዙ፤ በተለያዩ ሃገራት እስር ቤቶች እየተሰቃዩ ነውና ሌሎችም ዜናዎች ይሰማሉ።
በቅርቡም ከትግራይ ክልል ኢሮብ ወረዳ ከሊቢያ ተነስተው ሜዲትራንያንን ሊያቋርጡ የነበሩ 15 ወጣቶች ህይወታቸው አልፏል።
ወጣቶቹ በኢሮብ ወረዳ እንዳልገዳ በሚባል ቀበሌ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የነበሩ ሲሆኑ በህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ተታልለው ወደ ስደት እንዳመሩ የቀበሌው አስተዳዳሪ ብርሃነ አውአላ ተናግረዋል።
ሥርዓተ ቀብራቸውም ከትናንት በስቲያ ሐምሌ 30፣ 2011 ዓ.ም በቀበሌያቸው ተፈፅሟል።
ወጣቶቹ የእንዳልገዳን መንደር መቼ እንዳቋረጡም ይሁን እንዲሁ ስለ ሞቱበት ቀን የተሰጠ መረጃ የለም። የአካባቢው ማህበረሰብ መርዶውን የተረዳው ከአደጋው ከተረፉ ግለሰቦች ሰኞ እለት ሲሆን ዘጠኝ ሴቶችና ስድስት ወንድ ታዳጊዎች አደገኛውን የሜድትራንያን ባህር ሊያቋርጡ ሲሉ መሞታቸው ታውቋል።
አብረው የተጓዙት ተማሪዎች 19 የነበሩ ሲሆኑ ለወሬ ነጋሪ የተረፉት አራቱ ብቻ እንደሆኑ አስተዳዳሪው ገልፀዋል።
በሊቢያ ውስጥ በነበሩበት ቀናት ታግተው እንደነበር የቀበሌው አስተዳዳሪ ገልፀው ዘመዶቻቸው እነርሱን ለማስለቀቅ እስከ 300 ሺህ ብር መክፈል ነበረባቸው ሲሉ ያስረዳሉ።
በ1994 ዓ.ም ከኢሮብ ተነስተው ጂቡቲን አቋርጠው ወደ የመን ለመግባት ሲሞክሩ 14 ወጣቶች ባህር ላይ ሞተዋል።
በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ ከጂቡቲ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ሰጥማ ከስልሳ በላይ ከአፅቢ ወረዳ የመጡ ሰዎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል።