ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኒፕሲ ሐስል፡ በአባቱ ኤርትራዊ የሆነው ራፐር በሎስ አንጀለስ ተገደለ
የሎስ አንጀለሱ ታዋቂ ራፐር፣ ኤርምያስ አስገዶም (ኒፕሲ ሐስል) በተከፈተበት ተኩስ ሎስ አንደለስ ውስጥ መገደሉን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።
የ33 ዓመቱ ራፐር በርካታ ቦታዎች ላይ በጥይት መመታቱን እና ሆስፒታል እንደደረሰ ሕይወቱ ማለፉን ሎስ አንጀለስ ታይምስ ዘግቧል።
ሌሎች ሁለት ሰዎችም በተተኮሰባቸው ጥይት ቆስለዋል።
ከኤርትራዊ አባት እና ጥቁር አሜሪካዊ እናት የተወለደው ኤርሚያስ አስገዶም በዚህ ዓመት ለሽያጭ ያበቃው አልበሙ በግራሚ የምርጥ ራፕ አልበሞች ምርጫ ላይ እጩ ለመሆን በቅቶ ነበር።
የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚንስትሩ የማነ ገ/መስቀል የኤርሚያስ አስግዶም ሞት እጅጉን እንዳሳዘናቸው ያሰፈሩ ሲሆን ለቤተሰቦቹመ መጽናናት ከተመኙ በኋላ ኤርሚያስ ከአንድ ዓመት በፊት ሃገሩን ጎብኝቶ ነበር ሲሉ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
ሞቱ ካስደነገጣቸው ታዋቂ ሰዎች መካከል ፋራል ዊሊያምስ እና ሪሃና ይገኙበታል። ሪሃና "በዚህ ዜና መንፈሴ ታውኳል" ስትል የቲውተር ገጿ ላይ አስፍራለች።
ኤርሚያስ አስገዶም ተወልዶ ያደገው በደቡባዊ ሎስ አንጀለስ ሲሆን በተለያዩ የማህበረሰብ አቀፍ ስራዎችና በኪነጥበብ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ይታወቃል።
"ያደኩት በውንብድና ቡድኖች ውስጥ ነው" ሲል ለሎስ አንጀለስ ታይምስ በአንድ ወቅት ቃለ መጠይቅ ሰጥቶ ነበር "... ሞት፣ ግድያ የየእለት ትዕይንቶቻችን ነበሩ። በጦርነት ቀጠና ውስጥ እንደመኖር ነው፤ ከዚህ መንደር ሰዎች ሲሞቱ ከቁብ አይቆጠርም ነበር።"
ኤርሚያስ ከመገደሉ በፊት በነበረ አንድ እሁድ "አምርሮ የሚጠላህ ሲኖር መባረክ ነው" በማለት በቲውተር ገፁ ላይ አስፍሯል።