በአሜሪካ ሀሰተኛ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች መታሰር በሕንድ ቁጣን ቀሰቀሰ

በአሜሪካ 129 የህንድ ተማሪዎች መታሰራቸዉን ተከትሎ ደልሒ በሚገኘዉ የአሜሪካ ኤምባሲ ከፍተኛ ተቃዉሞ ተካሔደ።
ባለፈዉ ረቡዕ የአሜሪካ መንግስት ህጋዊ ካልሆነ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ አገኘኋቸዉ ያላቸዉን 129 ሕንዳዉያን ተማሪዎችን አስሯል።
ሚቺጋን ግዛት የሚገኘዉ ፋርሚንግተን የተባለዉ ዩኒቨርሲቲ የሀገር ዉስጥ የደህንነት መስሪያ ቤት ዉክልና አለኝ በማለት በህገወጥ መልኩ ወደ አሜሪካ የገቡ ተማሪዎችን ሲመዘግብ መቆየቱን መንግስት ደርሸበታለሁ ብሏል።
በተለይ ተማሪዎቹ በአሜሪካ እንዲቆዩ "ለመኖር መክፈል" በሚል እሳቤ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን 8500 እና የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን 11000 ዶላር አመታዊ ክፍያ ያስከፍል ነበር።
የሀሰት ዩኒቨርሲቲዉ በህገወጥ መልኩ ከተለያዩ ሀገራት ወደ አሜሪካ የገቡ ዜጎችን ታላሚ አድርጎ በጎርጎሳያውያኑ 2015 የተቋቋመ ነዉ። እናም ባለፈዉ ረቡዕ የአሜሪካ መንግስት ከዚሁ የሀሰት ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ አገኘኋቸዉ ያላቸዉን 129 ሕንዳዉያንን ጨምሮ 130 ተማሪዎችን አስሯል።
ተማሪዎቹን ለማስፈታት ቅዳሜ ህንድ ደልሂ በሚገኘዉ የአሜሪካ ኤምባሲ በመሰባሰብ ህንዳዉያን ተቃዉሟቸዉን አሰምተዋል።
ኤምባሲዉ በበኩሉ የተካሄደዉን የተቃዉሞ ሰልፍ እዉቅና ቢሰጥም ስለጉዳዩ ግን ያለዉ ነገር የለም። የህንድ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰልፉ የታሳሪዎቹን ደህንነት እና አማካሪ የማግኘት መብታቸዉን ለማስከበር ታስቦ የተደረገ መሆኑን ገልጿል።
ራሱን እንደህጋዊ ተቋም በተለያዩ አማራጮች የሚያስተዋዉቀዉ ፋርሚንግተን ዩኒቨርሲቲ በድረ ገፁ ተማሪዎች ክፍል ዉስጥ ሲማሩ ፤ ቤተመጽሃፍት ሲያነቡ እና በሳራማ ግቢ ሲዝናኑ በፎቶ ያሳያል።
ወቅታዊ ጉዳዮችን የሚያስተዋዉቅበትም የሀሰት የፌስቡክ ገጽ አለዉ። ነገር ግን ባለፈዉ ሳምንት ከፍርድ ቤት የወጣ መረጃ እንደሚያሳዉ የዩኒቨርሲቲዉ ሰራተኞች የኢምግሬሽንና የጉምሩክ ሰራተኞች እንጂ መደበኛ ሰራተኞች እንዳልሆኑ አረጋግጧል።
መንግሥትም ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲዉ ህጋዊ አለመሆኑን እያወቁ የተመዘገቡ በመሆናቸዉ በህግ እንዲጠየቁ አደርጋለሁ ብሏል። የህንድ መንግሥት ግን ዜጎቼ በፍጹም ይህን አያደርጉም በወንበዴዎች ተታልለዉ በመሆኑ ምህረት ሊደረግላቸዉ ይገባል በማለት ተማጽኗል።
በተለይ ተማሪዎቹ ያሉበት ሁኔታ እንዲገለጽ፤ ቀድመዉ ከእስር እንዲለቀቁ እና ከአሜሪካ እንዳይባረሩ የአሜሪካን መንግሥት መጠየቁን የህንድ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አስታዉቋል።

ከተማሪዎች በተጨማሪ 8 ሰዎች ስደተኞችን ለትርፍ በመጠቀም እና በቪዛ ማጭበርበር ወንጀል ተከሰዋል። እነዚህ ግለሰቦች በተለይ ተማሪዎችን በመመልመልና በማግባባት ከፍተኛ ሚና ነበራቸዉ ተብሏል።
በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት በስደተኞች ጉዳይ ጥብቅ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
በተመሳሳይ ከሶስት አመት በፊት ስደተኞችን መሰረት ያደረገ የሃሰት ዩኒቨርስቲ በመገኘቱ ብዙዎቹ ከቻይና እና ከህንድ የሆኑ 21 ሰዎች በሰሜን ኒዉ ጀርሲ ታስረዉ ነበር።
ባለፉት ሁለት የትራምፕ የአስተዳደር አመታት ደግሞ የብዙዎቹ ሰነድ አልባ እና ቪዛ ጠባቂዎች ጉዳይ እንዲዘጋ ተደርጓል።
በዚህ ሂደትም በርካታ የስራ ቦታዎች የእስረኞች መገኛ ሆነዉ ቆይተዋል። በሁለቱ የትራምፕ አመታት ብቻ የኢምግሬሽንና የጉምሩክ መስሪያ ቤት ኦሃዮ ዉስጥ ከሚገኝ አንድ የስጋ አቃራቢ ድርጅት 146 ሰዎችን እና ቴክሳስ ዉስጥ ከሚገኝ ሌላ ፋብሪካ ዉስጥ ደግሞ 150 ስደተኞችን በዚሁ ምክንያት አስሯል።












