"ከሞቱት አንለይም" የሶማሌ ክልል እስረኞች

የፎቶው ባለመብት, Human Rights Watch
በእስር ቤቱ የሚወልዱ እናቶች በሙሉ የህክምና አገልግሎት አያገኙም የምትለው የ31 ዓመቷ የሶማሌ ክልል የቀድሞ ታራሚ አያን "ሴት እስረኞች እርስ በርስ መረዳዳት ያለን ብቸኛ አማራጭ መሆኑን ባውቅም የመውለጃዬ ጊዜ ሲደርስ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡኝ ጠየቅኩኝ። የክልሉ ልዩ ፖሊሶች ግን የሰጡኝ ምላሽ ግን ልጁ አድጎም ስለማይረባ ሽንት ቤት ጣይው የሚል" እንደሆነ ትናገራለች።
የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር ደጋፊ ስለሚሆን መሞት እንዳለበት የነገሯት ታራሚም ተስፋ ባለመቁረጥ ሆስፒታል ውሰዱኝ ስትላቸው ምላሻቸው ሳቅ እንደነበር ትናገራለች።
"ተጨማሪ ውሀም ሊሰጡኝም አልቻሉም" ትላለች። እዚያው አስር ቤት በአስቸጋሪ ሁኔታ የተገላገለችው አያን የልጁንም እትብት ለመቁረጥ ስለት ያለው ብረት ከአካባቢያቸው መፈለግ ነበረባቸው።
ይህ የአያን ታሪክ የተወሰደው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው ሂውማን ራይት ዋች "ዊ አር ላይክ ዘ ዴድ" (ከሞቱት አንለይም) በሚል ርዕስ ዛሬ ካወጣው ሪፖርት ሲሆን በሶማሌ ክልል ኦጋዴን እስር ቤት የሚደርሰውን የዘፈቀደ እስራት፣ መደብደብ፣ መደፈርና የሰው ልጅ ማሰብ ከሚችለው በላይ እንግልትን ያጋለጠ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስቸኳይ ምርመራ እንዲጀምሩ የሚጠይቀው ሪፖርቱ የክልሉን የፀጥታ ኃይሎች እንዲቆጣጠሩና ባለሥልጣናቱም ተጠያቂነት ሊኖራቸው የሚያስችል ሥርዓት እንዲዘረጋና እርምጃ እንዲወስዱም አፅንኦት ይሰጣል።
በዚህ 88 ገፅ ባለው ሪፖርት እስረኞች የሚደርስባቸውን ስቃይ፣ እንግልት፣ መደፈር በተጨማሪ የህክምና እጦት፣ ረሃብ እንዲሁም ቤተሰብም ሆነ ጠበቃዎቻቸው እንዳያዩዋቸው እንደተደረጉም እስረኞቹ ለድርጅቱ እንደገለፁ ሪፖርቱ ያስረዳል።
በሪፖርቱ መሰረት ይህንን ሲፈፅሙ የነበሩት የእስር ቤቱ የሥራ ኃላፊዎችና የፀጥታ ኃይሎች፤ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Human Rights watch
እነዚህ ቡድኖች በሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሀመድ ኦማር ስር የሚገኙ ሲሆን ብዙዎቹም ከኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ስቃይ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
ግንባሩ በኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁ ቡድኖች መካከል አንዱ መሆኑ የሚታወስ ነው።
መንግሥት አድርጎ በማያውቀው ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ውስጥ በእስረኞች ላይ ስለሚደርሰው እንግልትና ስቃይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማስረዳታቸው የሚታወስ ነው።
በሶማሌ ክልል እየደረሰ ስላለው እንግልትም ሆነ ተጠያቂነት ስለሚረጋገጥበትም ሆነ ስለተጠቂዎቹ ፍትህ ዝርዝር ጉዳይ ግን አልተናገሩም።
ይህ ሪፖርት ሂውማን ራይትስ ዋች በሶማሌ ክልል የሚገኙ 100 የፀጥታ ኃይሎችን ጨምሮ የመንግሥት ባለሥልጣናትንና በባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ስቃይና እንግልት የደረሰባቸውን 70 ግለሰቦችን መጠይቅ አድርጎ ያጠናቀረው ነው።
"ለሦስት ዓመታት በጨለማ ቤት ተዘግቶብኝ ነው የኖርኩት" የሚለው የቀድሞ እስረኛ "በየቀኑ ማታ ማታ እደበደባለሁ። የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ያላደረሱብኝ ነገር የለም የዘር ፍሬዬን በኤሌክትሪክ ማቃጠልና በኤሌክትሪክ ሽቦ መጠፈር፣ በጭንቅላቴም ላይ በርበሬ ጨምረው በፌስታል ያፍኑኛል። እንዳልጮህም በጨርቅ አፌን ይጠቀጥቁት ነበር" ብሏል።
ራቁታቸውን በእስረኞች መካከል እንዲረማመዱ ማድረግ፣ እስረኞን ማደባደብና የሚያሸማቅቁ ተግባራትን እንዲያከናውኑ እንደሚያደርጓቸውም ታራሚዎቹ ተናግረዋል።
"በአንድ ወቅት በሁሉም እስረኞች መካከል ራቁቴን በጭቃ ላይ እንድንከባለል አዘዙኝና በዱላ ይደበድቡኝ ጀመር" የምትለው የ40 ዓመቷ ሆዳን ስትሆን ያለምንም ክስ አምስት ዓመታትን በእስር አሳልፋለች።
"በሌላ ጊዜም እንዲሁ አንድ በእድሜ ሸምገል ያሉ ሰውዬን ከሴት ልጃቸው ጋር ራቁታቸውን እንዲቆሙ አድርገዋቸዋል። በጣም የሚያሳፍር ነገር ነው" ትላለች።
እስረኞቹ እንደሚሉት የእስር ቤቶቹ ኃላፊዎች፣ የልዩ ፖሊስ ከፍተኛ ኃላፊዎች እንግልቱን፣ መደፈሩን፣ ምግብ ክልከላውን ከማዘዝ በተጨማሪ ተሳታፊም ነበሩ ይላሉ።
በተጨናነቁት በእነዚህ እስር ቤቶች ውስጥ በሚፈጠር ረሃብ፣ በሽታና ስቃይ ምክንያት ብዙዎችም ለሞት እንደተዳረጉ ሪፖርቱ ጨምሮ ያትታል።












