ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢራቅ አይ ኤስ 200 የጅምላ መቃብሮችን ትቶ መሄዱን የተባበሩት መንግሥታት ተናገረ
በኢራቅ እስላማዊ ቡድኑ አይ ኤስ ይቆጣጠራቸው በነበሩ አካባቢዎች ከ200 በላይ የጅምላ መቃብሮችና በሺዎች የሚቆጠሩ አስክሬኖች ማግኘቱን የተባበሩት መንግሥታት አጥኚ ቡድን ገለጠ።
መቃብሮቹ እስከ 12000 አስክሬን ድረስ እንደያዙ አጥኚው ቡድን ይፋ አድርጓል።
እስላማዊ ቡድኑ ከፊል ኢራቅን በቁጥጥሩ ስር አውሎ የነበረው በ2014 ሲሆን ጨካኝ አገዛዝን በማስፈንና የሚቃወሙትን በመግደል ይታወቃል።
የኢራቅ ጦር በአሜሪካ የአየር ጥቃት ተደግፎ ባካሄደው ዘመቻ አይ ኤስ ከበርካታ ቦታዎች ለቅቆ የወጣ ሲሆን በአንዳንድ ስፍራዎች ግን አሁንም ይንቀሰቀሳል።
አሁን የተገኙት የጅምላ መቃብር ስፍራዎች ሟቾችን ለመለየት ብቻ ሳይሆን በሰብዓዊነት ላይ የደረሱ ግፎችን፣ የተፈፀሙ የጦር ወንጀሎችንና የዘር ማጥፋት እርምጃዎች ላይ ክስ ለመመስረት የሚያስችሉ መረጃዎች ይሆናሉ ተብሏል።
እንደ ተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ከሆነ እስካሁን 202 የጅምላ መቃብሮች የተገኙ ሲሆን ከእነዚህም 95ቱ በናይንቫህ፣ 37ቱበኪርኩክ፣ 36ቱ በሳላህ አል ዲን እና 24ቱ በአንባር ናቸው።
መርማሪ ቡድኑ ከ6000-12000 ሟቾች በጅምላ መቃብሩ ተቀብረው እንደሚገኙ የገመቱ ሲሆን፤ ሴቶች፣ ህፃናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች፣ የኢራቅ የፀጥታ ኃይሎችና የውጪ ሀገር ዜጎች ከሟቾቹ መካከል ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገምቷል።