ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በካሜሮን ከ70 በላይ ተማሪዎችና መምህራን ታገቱ
በምዕራብ ካሜሮን በርካታ ተማሪዎችና መምህራን ታግተው መወሰዳቸው ተነገረ።
ሰኞ ዕለት 79 ተማሪዎችና ርዕሰ መምህሯን ጨምሮ ሶስት መምህራን በካሜሮን ከምትገኘው ባሜንዳ ታፍነው መወሰዳቸውን የመንግስት ባለስልጣናት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ከታገቱት ተማሪዎች መካከል ዕድሜያቸው ከ10 - 14 የሚደርሱ ህፃናት የሚገኙበት ሲሆን ይማሩበት የነበረው ትምህርት ቤትም ፕሪስቤቴሪያን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይሰኛል።
የካሜሮን ጦር ሰራዊትን ያካተተ የፍለጋ ቡድን ልጆቹን ለማግኘት አሰሳ ላይ ነው።
የአካባቢው አስተዳደር የሆኑት አዶልፍ ሌሌ ላአፍሪክ ልጆቹን ያገቱት ተገንጣየይ ቡድኖች ናቸው ሲሉ ከስሰዋል።
ሁለቱ የእንግሊዘኛ ተናጋሪ ክልሎች ነፃነታቸውን እንዲያገኙ የሚፈልጉ አማፅያን ትምህርት የማቆም አድማ ጠርተው ነበር።
ነገር ግን አንድም አማፂ ቡድን ልጆቹን ያገትኩት እኔ ነኝ ሲል ኃላፊነቱን አልወሰደም።
ከአጋቾቹ በአንዱ እንደተቀረፀ የተገመተ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ እየተንሸራሸረ ይገኛል።
በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ በአንድ ጠባብ ክፍል ተፋፍገው የቆሙ ወንድ ህፃናት ተደናግጠው ካሜራውን የያዘው ግለሰብ ስማቸውን እና የመጡበትን አካባቢ እንዲናገሩ ሲጠይቃቸው ይሰማል።
እንዲሁም "ትናንት ማታ በአምባ ቦይስ ነው የተወሰድኩት። የት እንዳለሁ አላውቅም" የሚል አረፍተ ነገርም ያስደግማቸዋል።
አምባ የሚለው መጠሪያ ተገንጣዮቹ ቡድኖች ሊፈጥሩት የሚፈልጉት አምባዞኒያ የተሰኘው ሀገር በአጭሩ ሲጠራ ነው።
ከተማሪዎቹ አንዱ የሆነው አልጋ ስር ተደብቆ ሳይያዝ የቀረው ልጅ ለቢቢሲ እንደተናገረው አጋቾቹ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ከገቡ በኋላ ነገሮች በፍጥነት ነው የተከናወኑት።
"አንድ ጓደኛዬን ያለርህራሄ ሲደበድቡት ነበር። ድምፄን አጥፍቼ መቆየት ብቻ ነበር የፈለግሁት። አንዳንዶቹን እንደሚተኩሱና እንደሚመቷቸው ይናገሩ ነበር። ትልልቆቹን ልጆች ከበቧቸው ትንንሾቹን ከኋላ ነበር ያደረጓቸው።"
በትምህርት ቤቱ መምህርት የሆነችው ደግሞ "ወታደሮቹ ወደ ትምህርት ቤቱ ከገቡ በኋላ በቀጥታ ወደ ርዕሰ መምህርቷ ቢሮ አመሩ፤ ከዛም በሩን በኃይል በመገንጠል ገቡ። አሁንም ስብርባሪው አለ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
በትምህርት ቤቱ እና በአማፂያኑ መካከል አሸማጋይ የሆኑት ግለሰብ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ "አጋቾቹ ምንም አይነት ነገር አይፈልጉም። የጠየቁን ትምህርት ቤቱን እንድንዘጋ ብቻ ነው። ስለዚህ ትምህርት ቤቱን እንደምንዘጋ ቃል ገብተንላቸዋል" ብለዋል።
"ተማሪዎቹንና መምህራኖቹን ይለቋቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉም አክለዋል።
አማፂያኑ በሚንቀሳቀሱባቸው ስፍራዎች ተማሪዎች ሲታገቱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ 5 ተማሪዎች ታግተው የተወሰዱ ሲሆን አስካሁን ድረስ የደረሱበት አልታወቅም።
የካሜሮን አማፅያን እንደሚሉት የሀገሪቱ የትምህርት ስርዓት እንግሊዘኛ ተናጋሪ የሆኑትን ይጨቁናል ሲሉ ይከሳሉ።