የሰኔ 16ቱ ጥቃት ተጠርጣሪ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ፍርድ ቤት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሰጠ

በሰኔ አስራ ስድስቱ ጥቃት ከተጠረጠሩት መካከል አንዱ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ፖሊስ የሚያካሂደውን የምርመራ አጠናቆ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት ተጨማሪ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ሰጠ።

ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተፈጸመውን ቦምብ ጥቃት በማሰተባበር፣ በመምራትና ለቦምብ ፍንዳታ የሚሳተፉ አካላትን በመመልመል የተጠረጠሩት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ባልደረባ በነበሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤት የአንድ ሳምንት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሰጥቷል።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ አንደኛው የወንጀል ችሎት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የፈቀደው ፖሊስ አስር ተጨማሪ ቀናት ምርመራውን ለማጠናቀቅ ፍርድ ቤቱን ከጠየቀ በኋላ ነው። ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ ጊዜ በሦስት ቀናት አሳጥሮ ነው ሰባት ቀናት የፈቀደው።

ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል በአቶ ተስፋዬ ኡርጌ ቤት የተገኘው ቦምብ ሰኔ 16/2010 ዓ.ም ጥቃት ከተፈፀመበት ቦንብ አንፃር የቴክኒክ ምርመራ ውጤቱ እንዲቀርብ ያዘዘ ቢሆንም ፖሊስ የምርመራ ውጤቱ ባለመጠናቀቁ ውጤቱን ለማቅረብ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም የምርመራው ሂደት ስላለበት ደረጃ ማብራሪያ የጠየቀ ሲሆን ፖሊስ የመጨረሻ የቴክኒክ ምርመራ ውጤቱን አጠናቆ በቀጣይ ቀጠሮ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ተጠርጣሪውም በጉዳዩ ላይ ፍርድ ቤቱ ተደጋጋሚ የምርመራ ጊዜ በመስጠቱ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁን ተቃውመዋል።

ፍርድ ቤቱ ምርመራውን እያካሄደ ያለው ፖሊስ የምርመራውን ውጤት ለጥቅምት 12/2011 ዓ.ም እንዲቀርብ በማሳሰብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።