የጠፉት የኢንተርፖል ሹም ቻይና ውስጥ ተገኙ

ሰውየው የዓለም ፖሊስ (ኢንተርፖል) አለቃ ነበሩ። ባለፉት ቀናት ውስጥ ብን ብለው ጠፉ። እስከ ትናንት ድረስ እምጥ ይግቡ ስምጥ አልታወቀም ነበር። እንደተፈራው ቻይና ሰውየው እኔ ዘንድ ናቸው፤ የቻይናን ሕግ በመጣስ ወንጀልም እየመረመርኳቸው ነው ብላለች።

ሜንግ ሆንግዊ በመስከረም 25 የኢንተርፖል ዋና ጽሕፈት ቤት ከሚገኝበት ከፈረንሳይ ሊዮን ተነስተው ወደ ቻይና ነበር ያቀኑት። ከዚያ ወዲህ ደብዛቸው ጠፍቶ ቆይቷል።

ቀደም ባለው ሥልጣናቸው በቻይና የሕዝብ ደኅንንት ጽሐፍት ቤት ምክትል አስተዳዳሪ እንደነበሩ የሚነገረው አቶ ሜንግ ሆንግዊ ምናልባትም ቻይና ጠልፋቸው ይሆናል የሚል ግምት ተንሰራፍቶ ቆይቶ ነበር። እንደተፈራውም አልቀረም። ሰውየው ከሙስና ጋር በተያያዘ እጅግ ተፈላጊ ሰው ናቸው ብላለች፤ ቤጂንግ።

ትናንት እሑድ ኢንተርፖል ዋና ኃላፊው የት እንዳሉ ብቻም ሳይሆን ከሰውየው መልቀቂያም እንደደረሰው ተናግሯል። ይህን ተከትሎም ኪም ጆንግ ያንግ የተባሉትን ደቡብ ኮሪያዊ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አድርጎ ሹሟል።

የታሳሪው ባለቤት ወይዘሮ ግሬስ ሜንግ ለጋዜጠኞች እንደተናገረችው ለመጨረሻ ጊዜ ከባሏ በበፌስቡክ የደረሳት መልእክት የቢላዋ ምስል (emoji) እንደሆነ ተናግራለች።

በቻይና እውቅ ሰዎች፣ ቢሊየነሮችና የቀድሞ አስተዳዳሪዎች ድንገት ዱካቸው የሚጠፋበት አጋጣሚ የበዛ ነው።

ኢንተርፖል 192 አገራትን ያሳተፈ የፖሊስ ሥራን የሚሠራ ዓለም አቀፍ ተቋም ሲሆን በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን ከመከታተል ውጭ የራሱን ፖሊሶች ልኮ በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥልጣን የለውም።