በሰኔ 16ቱ ፍንዳታ ወቅት ጥቅም ላይ ከዋለው ቦምብ ጋር የሚመሳሰል ቦምብ በተጠርጣሪ ቤት ተገኘ- ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Mark Metcalfe
በሰኔ 16ቱ ፍንዳታ ወቅት ጥቅም ላይ ከዋለው ቦምብ ጋር የሚመሳሰል ቦምብ በተጠርጣሪ ቤት አገኘው ሲል መርማሪ ፖሊስ አስታውቋል።
መርማሪ ፖሊስ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርቦ በስድስት ተጠርጣሪዎች ላይ የደረሰበትን የምርመራ ደረጃ ለፍርድ ቤት ባስረዳበት ወቅት ነበር በተጠርጣሪ ቤት ተመሳሳይ ቦምብ ማግኘቱን ያስታወቀው።
በተመሳሳይ ሁኔታ ከሁለተ ቀናት በፊት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት በሰኔ 16ቱ የቦምብ ፍንዳታ ተጠርጥረው በምርመራ ላይ የሚገኙት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ቦምብና የጦር መሳሪያ እንደተገኘባቸው መርማሪ ፖሊስ ማስታወቁ ይታወሳል። በወቅቱ ሌሎች በቁጥጥር ስር ያልዋሉ የጦር መሳሪያዎችን ለመያዝም ጥረት እያደረገ መሆኑን መርማሪው ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቶ ነበር።
መርማሪ ፖሊስ ዛሬ የምርመራ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁሞ የኤፍ ቢ አይ የቴክኒክ ምርመራ ውጤቶቸን ለመቀበል ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል በማለት 14 ቀን ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቃ ግን ምረመራው ይህን ያህል ረዥም ጊዜ የሚወስድ ባለመሆኑ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ አያስፈልግም ሲሉ አስተባብሏል።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩበት ድርጊት በማስረጃ መረጋገጡን ፖሊስ እንዲያሰረዳ በጠየቀው መሰረት፤ ፖሊስ ጌቱ ግርማ መኖሪያ ቤት ውስጥ በሰኔ 16 የቦምብ ጥቃት ላይ የዋለው ቦምብ አይነት ጋር ተመሳሳይ ቦምብ ማግኘቱን ገልጿል።
አብዲሳ ቀነኔ የተባለው ተጠርጣሪም ሌላኛውን ተጠርጣሪ ከአቤት ሆስፒታል ለማስመለጥ ነርሶችን ሲያግባባ ነበር፤ ለዚህም መረጃ አለኝ ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ ቦምቡ ከመፈንዳቱ በፊት እና ከፈነዳ በኋላ የተለዋወጡት መረጃ አለኝ ብሏል።
ፍርድ ቤቱም የምርመራው ሂደት የተወሳሰበ መሆኑን በመጥቀስ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።
ከሰኔ 16ቱ የቦምብ ፍንዳታ ጋር በተገናኘ ተጠርጥራ በአማኑኤል ሆስፒታል ህክምና ላይ የምትገኘውን የህይወት ገዳን ምርመራን ማቋረጡንም ፖሊስ ለችሎቱ አሳውቋል።














