በሰኔ 16ቱ የቦምብ ፍንዳታ የተጠረጠሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ የጦር መሳሪያ ተገኘባቸው- ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Mark Metcalfe
በሰኔ 16 ቱን የቦምብ ፍንዳታ ተጠርጥረው በምርመራ ላይ የሚገኙት ተስፋዬ ኡርጌ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱት ግጭቶች እጃቸው እንዳለበት መርማሪ ፖሊስ ማስታወቁን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
ተጠርጣሪው ቦምብና የጦር መሳሪያ እንደተገኘባቸውም መርማሪ ፖሊስ አስታውቋል። ሌሎች በቁጥጥር ስር ያልዋሉ የጦር መሳሪያዎችን ለመያዝም ጥረት እያደረገ መሆኑን መርማሪው ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።
ሁለቱንም ወገኖች ማስረጃ ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤት ሌሎች ተጨማሪ ምስክሮችን ለመስማት የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የተጠርጣሪው ጠበቃ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ከዋሉ ከወር በላይ ጊዜ ቢሆናቸውም በዚህ ጊዜ ውስጥ ፖሊስ ምንም አዲስ ማስረጃ አላቀረበም፤ ግለሰቡ ተጠርጥረው የተያዙት ከቦምብ ፍንዳታው ጋር የተገናኘ ቢሆንም አሁን ግን እየተደመጠ ያለው ሌላ ወንጀል ነው በማለት ቅሬታቸውን አሰቀምጥዋል።
በዚህም ምክንያት ደንበኛው በዋስ ይለቀቁለት ዘንድ በመጠየቅ የመርማሪ ፖሊሱን ጥያቄ ተቃውመዋል።
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ አቶ ተስፋየ ኡርጌ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከባድ መሆኑን በማሳወቅ ጊዜ የሚወስድ ጉዳይ ሆኖ በመገኘቱ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮውን ሰጥቷል።















