የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል-አቀባይ፡ "ለደቡብ ሱዳን ሰላም የኢትዮጵያን ያህል የባጀ የለም"

የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር ቃል-አቀባይ በ2010 የተከናወኑትን አበይት ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶችን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ፤ በአሁኑ ወቅት አንዳንድ እድገቶችን መሰረት አድርገው በመገኛኛ ብዙሃን የሚሰሩ ዘገባዎች ሙሉውን ስዕል አይሰጡም ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር ቃል-አቀባይ አቶ መለስ ዓለም የደቡብ ሱዳን የሰላም ሥምምነት የደረሰበትን ደረጃ ኢትዮጵያ ጊዜ ሰጥታ የደከመችበትና የለፋችበት ትልቁ ስራ ነው ማለት ነው የገለጹት። "ዋነኞቹ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ መሪዎች ሬክ ማቻርና ሳልቫ ኪር ከአንድ ዓመት በላይ ላለመተያየት ወስነው ከቆዩ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሸምግልናና ጫና ነው ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ላይ በአንድ ክፍል በአንድ ጠረጴዛ፤ በአንድ ገበታ ላይ መቀመጥ የቻሉት" ብለዋል።

በሬክ ማቻርና ሳልቫ ኪር የቅርቡ ሰላም ስምምነት የተደረገው በሱዳን መዲና ካርቱም መሆኑ ይታወሳል።

ከአዲስ አበባው ውይይት በኋላ የተካሄዱት ስብሰባዎች በኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበር ለሆነችው ኢትዮጵያ የተሰጡ ኃላፊነቶች መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

ቃል አቀባዩ በአሜሪካ ምክር ቤት የጸደቀውን "የኤች አር 128" የውሳኔ ሃሳብ በማርቀቅ ጉልህ ሚና የነበራቸው ክሪስ ሚዝ አዲስ አበባ እንደሚመጡና ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰብዓዊ መብትና ከዴሞክራሲ አንጻር የተሰሩ ጅምር ስራዎችን በአካል የማየት ዕድል እንደሚኖራቸው አብራርተዋል።

ቃል-አቀባዩ ጨምረው እንደተናገሩት የቬትናም ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ ከነገ ጀምሮ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደርጋሉ።