ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በድሬዳዋ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አልታወጀም ተባለ
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከጥቂት ቀናት በፊት ከተማዋን የጸጥታ ስጋትና የኮማንድ ፖስት መቋቋምን በማስመልከት መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ እያነጋገረ ይገኛል።
ኮማንድ ፖስት ከተቋቋመ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል ማለት ነው በሚል ግራ መጋባትም የተፈጠረ ይመስላል።
ነገር ግን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ አብደላ አህመድ ለቢቢሲ ዛሬ በስልክ እንደተናገሩት ባለፉት ቀናት በታዩ የግጭት ዝንባሌዎች የተነሳ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ የከተማዋን ጸጥታና ደህንነት ለመጠበቅ እየተሞከረ እንደሆነና እንደወትሮው ሁሉ አስተዳደሩ ከመከላከያ ሰራዊት እና ከፌዴራል ፖሊስ በጸጥታ ካውንስል በኩል በቅንጅት እየሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።
"አዲስ ነገር አይደለም። በመደበኛነት አብረን ነው የምንሰራው" ሲሉም የጸጥታ ካውንስል አዲስ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ባለፉት ሁለት ሶስት ቀናት አስጊ የነበሩ ነገሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው "ምንም የከፋ ነገር የለም።" ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።
ስጋት ያሳደሩት ጉዳዮች በዝርዝር ምን እንደነበሩ ከቢቢሲ የተጠየቁት አቶ አብደላ ከመሬት ጋር ተያይዞ የተነሱ ጥያቄዎች ነበሩ ሲሉ በደምሳሳው አልፈውታል።
በሶማሊያና በኦሮሚያ የተከሰተው የድንበር ግጭት ወደ ድሬዳዋ እየተዛመተ እንደሆን የተጠየቁት ምክትል ከንቲባው "በዚያ ደረጃ የሚገለጽ ነገር የለም። ይሄ የውስጥ ችግር ነው፤ ኮሚቴ አቋቁመን እየፈታነው ነው።" ሲሉ ችግሩ ምንም የብሔር መልክ እንደሌለው አጭር አስተያየታቸውን ለቢቢሲ ሰጥተዋል።