ለሀያ ዓመታት ያልተነጋገሩት ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ ቤተሰቦች

ሺሻይ ወረስ እባላለሁ። ብዙዎች ግን ወዲ ትሩንጒ እያሉ ነው የሚጠሩኝ።

እናቴ አምስት ልጆች ወልዳለች። ሶስት ሴትና ሁለት ወንዶች። ሁሉም ኤርትራ ውስጥ ናቸው።

ሁለቱ ሲደውሉልኝ የተለየ ስሜት ወረረኝ።

ለሃያ ዓመታት ያህል ተገናኝተን አናውቅም።

ኤርትራ ውስጥ ያለ በኩር ወንድሜ ሶስት ልጆችን እናቴ አገር ልታሳያቸው ወደ ኢትዮጵያ ይዛቸው መጥታ ነበር። በዚያው ሶስቱ ልጆቹን ለሃያ ዓመታት ያህል ሳያያቸው ነው ያደጉት።

የስልክ መስመር ክፍት የተደረገ እለት ማታ 2፡40 አከባቢ መፅሃፍ እያነበብኩ ነበር። የመጀምርያው ጥሪ ሳላነሳው ተዘጋ።

ድጋሚ ተደወለና አነሳሁት፡

"ሄሎ" አለችኝ

"ማን ልበል" አልኳት።

መጀመሪያ የጋዜጠኛድምፅ ነበር የመሰለኝ።

"ፍርቱና ነኝ ከአስመራ" ስትለኝ ልቤ ቆመ። ስሜቴን መቆጣጠር አቃተኝ።

ምን እንደ ምላት ጠፋኝ። መስመሩም ይቆራረጥ ነበር።

በኋላ እየተሻሻለ መጣ፡ እኔም ተረጋግቼ ማነጋገር ቀጠልኩ።

ወንድሜንም አቀረበችልኝ።

"በቀጥታ ከአስመራ ነው ምትደውይው ?" ስል ጠየቅኳት።

"አዎ"

"በአካል እስክንገናኝ ድረስ እንኳን በስልክ ድምፅህን ሰማሁ።"

በዛች ቅፅበት ምን እንደተሰማኝ አላውቅም። በቃ የተለየ ስሜት ሰውነቴን ወረረኝ።

ያኔ እድሜዋ 44 የነበረው እናቴ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ "ልጆቼን ሳላያቸው ልሞት ነው ትል"ነበር።

አሁን ግን ደስታዋ ከልክ በላይ ሆኗል።