ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰልፍ "ሱሰኛው" ስለሺ
ስለሺ ሐጎስ ለሰልፍ ባይታወር አይደለም። በተለይም ለተቃውሞ ሰልፍ። እንዲያውም ሱሰኛ ሳይሆን አይቀርም። ባለፉት ዐሥርታት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በተደረጉ መንግሥትን የሚነቅፉና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን የሚያፋፍሙ ሰልፎች ላይ ሁሉ ተሳትፌያለሁ ይላል።
በሳቅ በተኳለ ንግግሩ እንደሚተርከው የቸርቸል ጎዳናን ታክኮ በሚገኘው የኢትዮ-ኩባ አደባባይ ቆሞ የቅዋሜ ድምፁን አስተጋብቷል፤ ከስድስት ኪሎ ተነስቶ አራት ኪሎ እስከሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረስ እጁን እያወናጨፈ ተጉዟል፤ ፍርሃት በደም ሥሩ ሲላወስ አስተውሎ ራሱን ታዝቧል፤ በዱላ ተቀጥቅጦ ሩሁን ስቷል፤ የሆስፒታል አልጋን ተለማምዷል፤ እስካሁን የዘለቀ ሕመምን ተቀብሏል።
አሁን በሰላሳዎቹ የዕድሜ አፅቅ ውስጥ የሚገኘው ስለሺ፥ በጉርምስናው ወራት በትውልድ ቀዬው መቂ ከተማ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ የተከናወኑትን ሰልፎች ያስታውሳል።
በተለይም በወርሃ ሚያዝያ በቅንጅት ለአንድነት እና ዲሞክራሲ ፓርቲ ደጋፊዎች የተከናወነው መስቀል አደባባይን እና ዙርያ ገባውን የሞላ ሰልፍ እጅጉን አስደምሞት ነበር።
"ሚያዝያ ሠላሳ የነበረውን የቅንጅት ሰልፍ በቴሌቭዥን መታደም እጅግ የሚያስቀና ነገር ነበረው" ይላል ለቢቢሲ።
ሰልፉ፣ የድጋፍ ወይስ የተቃውሞ?
ለስለሺ ከምርጫ 97 በኋላ ያሉት ተከታታይ ዓመታት የገዥው ፓርቲ ድምፅ ብቻ የተስተጋባባቸው፥ የገዥ ፓርቲ ድምፅ ብቻ የተፈቀደባቸው ሆነው ለመዝለቃቸው አንዱ ማሳያ ከአዲስ አበባ ትልልቅ አደባባዮች አንዱ የሆነው መስቀል አደባባይ ነው።
በእነዚህ ዓመታት መስቀል አደባባይ ከሃይማኖታዊ በዓላት በዘለለ፤ ኢህአዴግ "ደግፉኝ እያለ ከየቀበሌው በሚቀስቅሳቸው ሰዎች አጥለቅልቆ" ራሱን የሚያሞካሽበት መድረክ ሆኖ ነበር ይላል።
በመሆኑም ስለሺ በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን፥ በቀይ ሽብር ሰማዕታት ቤተ መዘክር፥ በዋናው አውደ ርዕይ ማዕከል እና የኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜያት የምጣኔ ሃብት እርምጃ ምልክት ተደርጎ በሚቆጠረው ቀላል የከተማ ባቡር መንገድ እቅፍ ውስጥ ወደተዘረጋው መስቀል አደባባይ ከረዥም ጊዜ በኋላ ጎራ ያለው በቅርቡ ነበር። በሰኔ 16ቱ ሰልፍ።
ሰልፉን በርካቶች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እና ለለውጥ እርምጃዎቻቸው ድጋፍን ለማሳየት እንደተከናወነ ሲገልፁ ማዳመጥ እንግዳ ባይሆንም፥ ለስለሺ ግን ይህ አገላለፅ የሰልፉን መንፈስ ሙሉ በሙሉ አይወክልለትም።
ለስለሺ ሰልፉ የድጋፍነቱን ያህል የተቃውሞም ጭምር ነው።
ለእርሱ መስቀል አደባባይ ላይ የተካሄደው ሰልፍም ይሁን አሁን በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የሚከናወኑ ሰልፎች አስኳላቸው ተቃውሞ ነው።
"ሕዝቡ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በነበረው የኢህአዴግ አስተዳደር ላይ ያለውን ቅሬታን፥ ብሶት እና ተቃውሞ ለመግለፅ የሚከናወኑ ሰልፎች ናቸው" ይላል። "ይሄንን ለመለወጥ የተነሳውን አንድ ሰው እና አጋሮቹ ለማበረታታት በዚህም ተቃውሞውን ለማጠናከር የሚደረጉ ሰልፎች ናቸው። ዐብይን መደገፍ ኢህአዴግን መደገፍ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ተሳስተዋል።"
ብዙ ከተባለለት ደማቅ ትዕይንት እና ከዚያም በኋላ አንኳሩ ዜና የነበረው የቦንብ ፍንዳታ የሚያስተምሩን አንኳር ነጥቦች አሉ ይላል ስለሺ።
"የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ብዙ ጥያቄ አላቀረበም። መንግሥትን እጅህን ዘርጋልኝ አላለም፤ እጅህን ሰብስብልኝ ነው ሲል የነበረው። አንደኛ ይህንን ማስተዋል ችያለሁ" የሚለው ስለሺ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ የወሰዷቸው እርምጃዎች በአብዛኛው ይሄንን ያለቅጥ ተዘርግቶ የነበረ የመንግሥት እጅ መሰብሰብ ነበር" ይላል።
"[ኮከብ ከሌለው] አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ እስከ ኦነግ ባንዲራ" ድረስ የተለያዩ የአስተሳሰብ ጽንፎችን የሚወክሉ ትዕምርቶች በሰልፉ ላይ ቢስተዋሉም፥ እነዚህን የአስተሳሰብ መስመሮች ባንፀባረቁ ተሰላፊዎች መካከል ምንም ዓይነት ግጭትም ሆነ ውጥረት ያለመከሰቱ የሚነግረን ነገር አለ ይላል ስለሺ።
"ተቃራኒ አስተሳሰቦቹን የሚያራምዱ ፖለቲከኞች ቁጭ ብለው መነጋገር የማይቻላቸው ቢመስልም፥ ደጋፊዎቻቸው ግን ተቃቅፈው ሁሉ መዘመር እንደተቻላቸው" ከጠቀሰ በኋላ "ይህም ብዙ አስተምሮኛል" ይላል።
በስለሺ ዕይታ ይህ ወደ ዲሞክራሲ ለሚደረግ ጉዞ የተመቸ ሕዝብ እንዳለ የሚጠቁም ነው።
ቅድመ ዐብይ ሰልፎች
ስለሺ በትምህርት ምክንያት ወደ መዲናዋ ከዘለቀ እና እርሱንም ተከትሎ ኑሮውን በቋሚነት ከመሠረተ በኋላ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሳተፍ የነበረውን ድባብ ሲያስታውስ ፈገግታ ያመልጠዋል።
በሁለት ሺዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ነው። ጉምቱዋ የተቃውሞ ፖለቲካ መሪ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለሁለተኛ ጊዜ ለእስር ተዳርገዋል፤ ይህ ያስቆጣቸው የአንድነት ፓርቲ አባላት ስሜታቸውን በአደባባይ ለመገልፅ ቆርጠዋል።
በምርጫ 97 በኋላ ከተደረጉት ቀዳሚ የተቃውሞ ሰልፎች አንዱን ለማከናወንም ፈቃድ አግኝተዋል።
ሦስት መቶ የማይሞሉ የፖርቲው አባላት ከፓርቲው ጽሕፈት ቤት ተነስተው እስከ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ድረስ የተቃውሞ ድምፃቸውን እያሰሙ ሲጓዙ ስለሺ ከመካከላቸው ነበር።
"በ97 ዓ.ም የነበረው ግድያ እና ደም አእምሯችን ውስጥ ስለነበር ስጋት ሰንጎን ነበር" ይላል።
"በማንኛውም ሰዐት ጥይት ሊተኮስ እንደሚችል እያሰብን ነበር የምንሄደው።"
ሰልፈኞቹ ወደ ቤተ መንግሥት እየተቃረቡ ሲመጡ በርከትከት ብለው የቆሙ ወታደሮች ስሜታቸውን የበለጠ እንደረበሹት የሚናገረው ስለሺ፥ ይሄኔ ከሰልፈኞቹ አንደኛው ሰልፉን በጠንካራ መፈክሮች ከሚመራውን ሰው የድምፅ ማጉያ ነጥቆ "እኛ ሰላማዊ ነን" የሚል መፈክር እንዲያሰማ እንዳስገደዱት ያስታውሳል።
ከዚያም በኋላ ተቃዋሚዎቹ ሰማያዊ እና አንድነት ፓርቲዎች ባዘጋጇቸው ሰልፎች ላይ የተሳተፈው ስለሺ፥ የአንድነት ለፍትህ እና ዲሞክራሲ ፓርቲ ልሳን የነበረች "የሚሊዮኖች ድምፅ" የተሰኘች ጋዜጣን ማዘጋጅትም ጀምሮ ነበር።
ፓርቲው የጠራውን ሰልፍ ለመዘገብ ከነ ፎቶ መቅረጫ በወጣበት አንድ ወቅት ለፖሊስ ዱላ መዳረጉን ይገልፃል።
"ካሜራየን ደብቄ ዞር ስል፥ አንድ ዱላ መትቶ ጣለኝ" ከዚያም "በርካታ ፖሊሶች ቀጥቅጠው ግራ እጄ እንዲሰብር አደረጉ፤ በብረት ነው ያለው። ብረቱ አሁንም ድረስ አለ" ሲል ይናገራል ስለሺ።
በድብደባው ምክንያት ስምንት ወር ይተኛ እንጂ እስካሁም በጣም የሚገርመው ግን በወቅቱ ከሠላሳ ለማይበልጡ ሰልፈኞች በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች መምጣታቸው መሆኑን ያስታውሳል።
የዐብይ መቶ ቀናት በስለሺ
ስለሺ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን ወደ መሪነት መምጣት እና እርሳቸውም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ በኋላ የወሰዷቸውን እርምጃዎች "የአብዮት ትርፉቶች" ናቸው ሲል ይገልፃቸዋል።
እናም "የኢትዮጵያ አብዮት ገና መጠናት አለበት።"
ይሁንና ስለሺ የቅርብ ጊዜ የቅርብ አገራትን ተሞክሮ ማጤን ለንፅፅር ይጠቅማል ባይ ነው።
"የሊቢያ አብዮት ጋዳፊን በመግደል ነው የተጠናቀቀው፤ የግብፅ አብዮት ሙባረክን በማሰር ነው የተጠናቀቀው።"
ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከነባር የኢህአዴግ አመራሮች መካከል ማንም ሳይሞት፥ ማንም ሳይታሰር "ኃሳባቸው ነው የሞተው" ይላል።
ለስለሺ እንደሚለው አይበለውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በመቶኛ ቀናቸው ድንገት ሥልጣን ቢለቁ እንኳ የእስካሁኑ እርምጃዎቻቸው በቂ ስኬትን ይዟል።
"ዐብይ ከዚህ በኋላ የሚመጣው ጠቅላይ ሚኒስትር ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት ልኬታ አስቀምጧል።"