ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከ20 ዓመታት በኋላ አዲስ ምዕራፍ ከፈቱ

የፎቶው ባለመብት, Fitsum Arega
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከሃያ ዓመታት በኋላ ኤርትራን ለመጎብኘት በመጓዝ ወደ አሥመራ ከገቡ በኋላ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መሪ ሆኑ።
ለዚህ ጉብኝት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋር የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የፌዴሬሽም ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ኬርያ ኢብራሂምና የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮ ሃላፊው አቶ አህመድ ሽዴ አብረዋቸው ተጉዘዋል።
ለጉብኝቱ የኤርትራ መንግሥት ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥቶ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በተለያዩ ከተሞች ከባለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሥመራ ሲደርሱ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና ከፍተኛ የኤርትራ ባለስልጣናት በአየር ማረፊያው ተገኝተው አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ጎዳና ላይ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ለጠቅላይ ሚኒስትሩን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ለጠቅላይ ሚኒስተሩ አቀባበል ለማድረግ በአስመራ ጎዳናዎች ላይ ከወጡት ተሳታፊዎች መካከል አንዱ "የኤርትራ ህዝቦች ለሰላም ብዙ መሰዋዕትነት ከፍለዋል። ከ20 ዓመታት ድካምና ትዕግስት በኋላ የመሰዋዕታችንን ውጤት በዲፕሎማሲ፤ በሰላም ጥሪ እና በእድገት መልክ እያየነው ነው።'' በማለት የነበረውን ስሜት ገልጿል።
ሌላኛው የአስመራ ነዋሪ በበኩሉ "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ወንድሞቻቸውና ወደ ሃገራቸው ነው የመጡት። እኛ ለብዙ ዘመናት ስናልመው የነበረውን ሰላም እውን አድርገዋል። በብዙ ምክንያት ሳይሳካ የቀረውን ሰላም እንድናየው ረድተውናል። እንኳን ወደ አስመራ በደህና መጡ።'' ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, YEMANE GM
በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት እስጢፋኖስ አፈወርቂ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አቀባበል ደማቅነትን በተመለከተ ባሰፈሩት መልዕክት "በኤርትራ ታሪክ የዛሬውን ያህል ለየትኛውም የሃገር መሪ ጉብኝት የሞቀ አቀባበል ተደርጎ አያውቅም" ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ፍፁም አረጋ በበኩላቸው በትዊተር ገፃቸው ላይ እንዳሉት "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለታሪካዊው ጉብኝት አሥመራ ሲደርሱ በፕሬዝዳንት ኢሳያስና በበርካታ ሕዝብ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል" ሲሉ አስፍረዋል።
በናይሮቢ ከተማ የሚኖር መአሾ ሃበቴ ተስፋ ሚካኤል የተባለ ኤርትራዊ ''ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ሁሌም ቢሆን ጎረቤታሞች ናቸው፤ ጎረቤታሞች ሆነውም ለዘልአለም ይቀጥላሉ።'' ሲል ያለውን ተስፋ ገልጿል።
አክሎም በኤርትራ አንድ አባባል አለን፤ ''የምትተኛ ከሆነ ጎረቤትህም መተኛት አለበት''። በተፈጠረው ነገር ደስተኛ ነኝ። ለሁለቱም ሃገራት ሰላምን እመኛለው።'' ብሏል።
ኢትዮጵያ የአልጀርሱን የድንበር ኮሚሽን ውሳኔን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኗን ተከትሎ የተጀመረው የሁለቱን ሃገራት ግንኙነትን ለማሻሻል እየተደረገ ያለው ጥረት አንድ አካል የሆነው ይህ ጉብኝት ትልቅ እርምጃ እንደሆነ እየተገለፀ ነው።
በዚህ ጉብኝት የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ቀደም ሲል የተጀመሩ ንግግሮችን በመቀጠል ወደፊት ስለሚኖረው ግንኙነትና ትብብርን በተመለከተ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የፎቶው ባለመብት, Fitsum Arega












