"ወደ ቀድሞ ቀያቸው ተመልሰው ህይወታቸውን መምራት ይችላሉ"

ባለፈው ጥቅምት ወር በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሼ ዞን ተወላጆች እና ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ስፍራው በማቅናት ኑሯቸውን በመሰረቱ አርሶ አደሮች መካከል ግጭት ተቀስቅሶ ሞት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀልን አስከትሏል።
በግጭቱ ምክንያት ከተፈናቀሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች መካከል ከአምስት መቶ የሚልቁ አባወራዎች በባህር ዳር ከተማ ተጠልለው ይገኛሉ።
ህዝቡን የማረጋጋት ሥራ እየተሰራና ለተጎዱ ቤተሰቦች እርዳታ እየተደረገ ሲሆን አደጋ ያደረሱ 65 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው በክስ ሂደት ላይ እንደሚገኙ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ከዚህ ቀደምም ተከታታይ ግጭቶች እንደተፈጠሩና ባለፈው ጥቅምት ላይ በተከሰተው ግጭት አመራሮችን ጨምሮ 65 ሰዎች ማረሚያ ቤት እንደሚገኙ ገልፀዋል።
"አሁንም በብሔሮች መካከል ግጭቶችን የሚፈጥሩ፣ ግለሰቦችን እየለዩ ጥቃት የሚያደርሱና ሌሎች ያለአግባብ እንቅስቃሴዎችን የሚያደረጉ ሰዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ክልሉ ተግቶ ይሰራል" ብለዋል።
በቅርቡ በተከሰተው ግጭትም እጃቸው አለበት የተባሉ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው በክስ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
የተፈናቀሉትም "ወደ ቀድሞ ቀያቸው ተመልሰው ህይወታቸውን መምራት ይችላሉ" በማለት አቶ አሻድሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከተፈናቃዮቹ መካከል ወደ ቀድሞ ቀያቸው የተመለሱም እንዳሉ ገልፀው ቀሪዎቹም ቢመለሱ በሰላም ከህብረተሰቡ ጋር መኖር የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በባህርዳር ከተማ በቤተ-ክርስቲያን ተጠልለው የሚገኙት ተፈናቃዮች የአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁንና ሌሎች ሃላፊዎች እንዲመለሱ ቢያነጋግሯቸውም አሁንም ስጋት ስላላቸው መመለስ እንደማይፈልጉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።












