ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አዲሱ መድኃኒት ራሰ በራዎችን ይታደግ ይሆን?
ራሰ በራነት የሚያስጨንቃቸው ሰዎች የራስ ቅላቸውን በጸጉር ለመሸፈን የተለያዩ መድኃኒቶች ይሞክራሉ። አዳዲስ መድኃኒቶች ገበያውን ሲቀላቀሉም ሸማቻቸው ብዙ ነው።
ቀደም ሲል ራሰ በራነትን ይፈውሳሉ ከተባሉ መድኃኒቶች በላቀ ውጤታማ እንደሚሆን ተስፋ የተጣለበት አዲስ መድኃኒት ይፋ ተደርጓል።
መድኃኒቱ የተሰራው ጸጉር በማሳደግ ምስጉን ከሆኑ ንጥረ ነገሮች መሆኑ ተመልክቷል። የአጥንት መዳከም በሽታን (ኦስትዮፕሮሲስ) ለማከም የሚውል ንጥረ ነገር ይገኝበታል።
ሳይክሎስፖሪን ኤ የተሰኘው መድኃኒትና ኤስኤፍአርፒዋ-1 የተሰኘው ፕሮቲን ጸጉር በማሳደግ ስለሚታወቁ በአዲሱ መድኃኒት ተካተዋል። መድኃኒቱ ዌይ-316606 በተባለ ንጥረ ነገርም ተሞልቷል።
የመድኃኒት ቅመማ ፕሮጀክቱ መሪ ዶ/ር ናታን ሀውክሻው ለቢቢሲ እንደተናጉት "መድኃኒቱ ጸጉራቸውን ያጡ ሰዎችን ህይወት ሊቀይር ይችላል" በማለት የመድኃኒቱን ፍቱንነት ለመፈተሽ ተጨማሪ ሙከራዎች እንደሚጠብቋቸውም ገልፀዋል።
ፒኤልኦኤስ በተሰኘው የሥነ-ህይወት መጽሔት ላይ የወጣው ጥናት እንደሚያሳየው፤ መድኃኒቱን ለመቀመም የጸጉር ቀዶ ህክምና ለማድረግ እየተጠባበቁ የነበሩ 40 ወንዶች ከራስ ቅላቸው የህዋስ ናሙና ሰጥተዋል።
የእንግሊዝ የቆዳ ሀኪሞች ማህበር ቃል አቀባይ ጥናቱን "ግሩም" ሲሉ ገልፀውታል።
"የጸጉር መሸሽ በራስ መተማመንን ዝቅ በማድረግ ሥነ-ልቦናዊ ተፅእኖ ያሳድራል።" የሚሉት ቃል አቀባዩ መድኃኒቱ አገልግሎት ላይ ከመዋሉ በፊት ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም በርካታ የራሰ በራነት መድኃኒቶች መክሸፋቸውን በማስታወስ "እስከአሁን ዓለም አቀፍ የሆነ ውጤታማ መድኃኒት የለም" በማለት ያስረዳሉ።
አዳዲስ ጥናቶች መካሔዳቸውና መድኃኒቶች መቀመማቸው፣ ለራሰ በራዎች ተስፋ ሰጪ ከመሆኑ ጎን ለጎን የህክምና አማራጭን እንደሚያሰፋም ተናግረዋል።
አሁን ገበያ ላይ ያሉት መድሀኒቶች ለሴቶችም ለወንዶችም የሚሆነው ሚኖክሲዲልና ወንዶች ብቻ የሚጠቀሙበት ፊናስትራይድ ናቸው።
ሁለቱ መድኃኒቶች ለጤና እክል ስለሚዳርጉ ብዙዎች ጸጉር ለማግኘት ቀዶ ጥገና ማድረግ ይመርጣሉ።