ሳሙኤል ኤቶ ለቀድሞው የብሄራዊ ቡድን አምበል ቤት ሊገዛ ነው

የፎቶው ባለመብት, Samuel Eto'o Fils/Steve Djouguela
የቀድሞው የካሜሩን ብሄራዊ ቡድን አምበል ኖርበርት ኦዎና በከባድ የኑሮ ጫና ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት ቤት አልባ ሆኖ ቢቆይም፤ ታዋቂው እግር ኳሰኛና የሃገሩ ልጅ የሆነው ሳሙሴል ኤቶ አለሁልህ፤ እኔ አዲስ ቤት እሰጥሃለው ብሎታል።
ኤቶ ለቢቢሲ እንደተናገረው በቅርቡ ወደ ሃገሩ በተመለሰበት ወቅት ነው ኖርበርትን ያገኘው።
የቀድሞው የባርሴሎና እና ቼልሲ አጥቂ ሳሙኤል ኤቶ በአሁን ለኳታር ስፖርትስ ክለብ የሚጫወት ሲሆን፤ የ67 ዓመቱን የቀድሞ ብሄራዊ ቡድን አምበል የጎዳና ህይወት የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም በሃገሪቱ ቴሌቪዥን ከተመለከተ በኋላ ነው ሃሳቡ የመጣለት።
ኦዎና ሆስፒታል ውስጥ የአንጀት ቀዶ ጥገና ለማድረግ እየተጠባበቀ ሲሆን፤ ቢቢሲ በስልክ ባነጋገረው ወቅትም ኤቶ በጣም ሩህሩህና ቅን ሰው እንደሆነ ተናግሯል።
የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ አራት ጊዜ የተመረጠው የ37 ዓመቱ ሳመኑኤል ኤቶ 1000 ዶላር እንደሰጠውና በተጨማሪም አዲስ የመኖሪያ ቤት ለመስጠት ቃል እንደገባለት አክሏል።
የኦዎናን ህይወት በሚያሳየው ዘጋቢ ፊልም ላይ የቀድሞ እግር ኳሰኛ የነበረውን ጥሪት በሙሉ አሁን በህይወት የሌሉትን ልጁን እና ባለቤቱን ለማሳከም እንዳዋለው ተናግሯል። በመጨረሻም ወደ ጎዳና ህይወት ለመውጣት እንደተገደደና የሚበላው እስከማጣት እንደደረሰ ይናገራል።
ዘጋቢ ፊልሙ አየር ላይ ከዋለ በኋላ ግን የሃገሪቱ ቀዳማዊ እመቤት ቻንተል ቢያን ጨምሮ ብዙ ካሜሮናውያን ሆስፒታል ገብቶ ህክምና እንዲከታተል ረድተውታል።
ሌላኛው የቀድሞ የካሜሩን ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ጆሳፍ ካምጋ እንደሚለው ኦዎና ብቻ ሳይሆን ለሃገራቸው ታሪክ የሰሩ ብዙ ካሜሩናውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች ተረስተዋል። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።
የካሜሩን እግር ኳስ አካዳሚ በበኩሉ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋቾችን ወደ አሰልጣኝነትና ወደ አመራር ቦታ ለማምጣት እቅድ ነድፎ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።












