ቀጣዩ የፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ማን ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እ.አ.አ በ2009 ማንቸስተር ዩናይትድ በተከታታይ አሸናፊ ከሆነ በኋላ የትኛውም የእንግሊዝ ቡድን በተከታታይ ዓመታት የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ አንስቶ አያውቅም። ይሄ ዓመት የተለየ ነገር ያሳየን ይሆን?
በስፔን ላሊጋ እንዲሁም በጀርመን ቡንደስሊጋ ባርሴሎናንና ባየር ሙኒክን ይዞ ለተከታታይ ሶስት ዓመታት የሊጎቹ አሸናፊ መሆን የቻለው የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ዋና አላማ ደግሞ ይህንን ታሪክ በእንግሊዝም መድገም ነው።
በመጪው አርብ በሚጀመረው የ2018-19 የእንግሊዝ ፕሪምር ሊግ የትኞቹ ቡድኖች ለዋንጫው ይገመታሉ? በክረምቱ የዝውውር መስኮት ብዙ ገንዘብ ወጪ ያደረጉት ሊቨርፑሎች ወይስ በሞሪንሆ የሚመራው ማንቸስተር ዩናይትድ?
ባለፉት ሁለት ዓመታት ድንቅ አቋም እያሳዩ ያሉት ቶተንሃሞች ወይስ አዲስ አሰልጣኝ የቀጠሩት አርሰናሎች?
በቢቢሲ የቴሌቪዥንና ራድዮ የስፖርት ፕሮግራም የሚያዘጋጁ 24 የእግር ኳስ ተንታኞች የትኛው ቡድን ያሸንፋል ብለው እንደሚገምቱ ተጠይቀው ያሸንፋል የሚሉትን ቡድንና ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል።
ማንቸስተር ሲቲ
ማን ያሸንፋል ተብለው ከተጠየቁት 24 እግር ኳስ ተንታኞች መካከል ሃያ አንዱ ማንቸስተር ሲቲ የ2018-19 የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ይሆናል ሲሉ የተቀሩት ሶስቱ ግን ሊቨርፑል ብለዋል።
ማንቸስተር ሲቲዎች ያለ ምንም ጥርጥር ለሁለተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ይሆናሉ የሚለው የቀድሞው የኒውካስል አጥቂ አለን ሺረር፤ ይህ ደግሞ የሚሳካው በአሰልጣኙ ፔፕ ጋርዲዮላ በሳል አመራር ብቻ ነው ሲል አስተያየቱን አስቀምጧል። ባለፈው ዓመት የተከተሉትን አጨዋወት የሚደግሙት ሲሆን፤ ሊቨርፑልና ማንቸስተር ዩናይትድ ግን ከባለፈው ወቅት በተለየ መልኩ በቅርብ ርቀት ይከተሏቸዋል ብሏል።
ሌላኛው ማንቸስተር ሲቲ በቀጣዩም ዓመት አሸናፊ ይሆናል የሚለው ደግሞ ማቲው አፕሰን ነው። እሱ እንደሚለው ማንቸስተር ሲቲዎች በደንብ እንደ ለሰለሰ ማሽን ናቸው። ''በባለፈው የኮሚዩኒቲ ሺልድ የዋንጫ ጨዋታ ወሳኝ የሚባሉት ኬቨን ደብራይነ እና ዴቪድ ሲልቫን እንኳን ሳይዙ ማሸነፍ ችለዋል። ስለዚህ ይህ ቡድን እጅግ የተሟላና በቀጣይም አሸናፊ የሚሆን ቡድን ነው።''

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሊቨርፑል
ባለፈው ውድድር ዘመን ሊቨርፑል ስንተኛ ሆኖ ይጨርሳል ተብለው ከተጠየቁ ሰዎች መካከል 13 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ነበሩ አራቱ ውስጥ ይገባል ብለው የገመቱት። በዚህ ዓመት ግን በአስገራሚ ሁኔታ 96 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች ምርጥ አራት ውስጥ ይጨርሳሉ ብለው ሲገምቱ፤ 14 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ዋንጫውን ያነሳል ብለዋል።
ሊቨርፑሎች የዘንድሮውን ዋንጫ እንደሚያነሱ ከፍተኛ ተስፋ ደረገው የቀድሞ የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ኮከብ ኢየን ራይት ነው። እንደ እሱ ሃሳብ ከሆነ ሊቨርፑሎች የታመቀ ጉልበት ባላቸው ወጣቶች የተሞላ ቡድን ነው። ምናልባትም ለዋንጫው ብዙ ግምት እያገኙ ያሉት ማንቸስተር ሲቲዎችን ሊያስጨንቋቸው የሚችሉት ሊቨርፑሎች ብቻ ናቸው ይላል።
ሊቨርፑሎች በፕሪምር ሊጉ ጥሩ ሲሆኑ አጠቃላይ የእንግሊዝ ፕሪምር ሊግ ይደምቃል ብሏል።
የዚህኛው ዓመት ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ሊቨርፑሎች ይሆናሉ ብሎ የሚያምነው ሌላኛው ተንታኝ ሩድ ጉሌት የየርገን ክሎፕ የአጨዋወት ስልት ከማዝናናት ባለፈ ውጤታማ ያደርጋቸዋል ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ዓመት ቢቢሲ ካነጋገራቸው የእግር ኳስ ተመልካቾች መካከል 33 በመቶ የሚሆኑት ዋንጫው የማንቸስተር ዩናይትድ እንደሚሆን ገምተው የነበረ ሲሆን፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ግን ሁለተኛ ሆኖ ጨርሷል። በዚህ ዓመት ግን የትኛውም ሰው ማንቸስተር ዩናይትድ ዋንጫውን ያነሳል ብሎ አያስብም።
ምንም እንኳን ማንቸስተር ዩናይትዶች ብዙ ኮከብ ተጫዋቾችን በቡድናቸው ውስጥ ቢይዙም ደጋፊዎቻቸውን የሚያስደስት ውጤትም ሆነ አጨዋወት ማሳየት ሳይችሉ ቀርተዋል። በሆዜ ሞሪንሆ ስር ግን በቡድኑ ውስጥ ብዙ ለውጦች እየታዩ ነው።















