ሳልቫዶር ራሞስ፡ አሜሪካ ቴክሳስ ውስጥ ለልደቱ በተገዛ ጠመንጃ 19 ሕጻናትን ጨምሮ 21 ሰዎችን የገደለው ወጣት

በአሜሪካዋ የቴክሳስ ግዛት አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የነበሩ 19 ሕጻናት ጨምሮ 21 ሰዎችን ተኩሶ የገደለው የ18 ዓመት ወጣት ሳልቫዶር ራሞስ እንደሚባል ፖሊስ አስታውቋል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረው ራሞስ ተኩስ ከፍቶ ሰዎችን ከመግደሉ በፊት ጥቃት ለማድረስ በዝግጅት ላይ መሆኑን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አመላክቶ ነበር ተብሏል።

"በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ተኩስ እከፍታለሁ" ብሎ የፌስቡክ ገጹ ላይ ጽፎ እንደነበረ የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግራል።

ይህ የ18 ዓመት ወጣት ጥቃት ወዳደረሰበት ትምህርት ቤት ሄዶ 21 ሰዎችን ከመግደሉ እና 17 ሰዎችን ከማቁሰሉ በፊት ሴት አያቱን ፊታቸው ላይ በጥይት መትቶ ገድሏል።

ራሞስ ተኮሱ የገደላቸው ሕጻናት ከ7 እስከ 10 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የ2ኛ፣ የ3ኛ እና የ4ኛ ክፍል ተማሪዎች ነበሩ።

ራሞስ ጥቃቱን እንዴት ፈጸመ?

ጥቃት ወደከፈተበት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትም የቤተሰቡን ባለጭነት መኪና እያሸከረከረ ሄዷል።

ማክሰኞ ከእኩለ ቀን በፊት ኤር-15 የተሰኘ መሳሪያውን ታጥቆ ወደ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ገባ። መርማሪ ፖሊስ እንዳለው ወጣቱ ጥቃት ለማድረስ ሲሄድ ከኤር-15 በተጨማሪ ሽጉጥም ይዞ ነበር።

የቴክሳስ ግዛት ኃላፊ ክርስቶፈር ኦሊቫሬዝ "ተጠርጣሪው ወደ ትምህር ቤቱ እንደገባ በፍጥነት ልጆችን፣ መምህራንን፣ ፊት ለፊቱ ባገኘው ላይ ሁሉ መተኮስ ጀመረ" ከክስተቱ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

የቴክሳስ ግዛት አስተዳዳሪ ግሬግ አቦት ጥቃት አድራሹ ወጣት ከፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት መገደሉን ገልጸዋል።

ጦር መሳሪያ ለ18ኛ ልደት በዓል

ራሞስ ይህን ጥቃት ለማድረስ የተጠቀመውን ኤራ-15 የተባለውን በከፊል አውቶማቲክ የሆነውን የጦር መሳሪያ ለ18ኛ የልደት በዓሉ ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ መግዛቱ ተገልጿል።

"በ18ኛ የልደት በዓሉ ካደረጋቸው መካከል አንዱ መሳሪያ መግዛት ነው" ብለዋል ክርስቶፈር ኦሊቫሬዝ።

የራሞስ ነው የተባለ የኢንስታግራም ገጽ፣ ወጣቱ በከፊል አውቶማቲክ ከሆነው መሳሪያ ጋር አብሮ የተነሳው ፎቶግራፍ አሳይቷል።

ራሞስ ጥቃቱን ከማድረሱ ከቀናት በፊት ለቀድሞ የክፍል ጓደኛው የገዛውን ጦር መሳሪያ እና በጥይት የተሞላ ቦርሳ ፎቶ አንስቶ መላኩንም ይኽው ጓደኛው ተናግሯል።

እኩዮቹ 'የሚያበሽቁት' ዓይንአፋር ተማሪ

ራሞስ ይህን ጥቃት ለመፈጸም ምን እንዳነሳሳው እስካሁን ግልጽ አይደለም።

የቴክሳስ ግዛት አስተዳዳሪዎችም ራሞስ የቀደመ የወንጀል ታሪክም ሆነ የአእምሮ ጤና መቃወስ አጋጥሞት አያውቅም ይላሉ።

ራሞስ የመጀመሪያ ደረጃት ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎች በተደጋጋሚ የበሽቁት፣ ይሳለቁበት ነበር።

ራሞስ ሲናገር ኮልታፋ በመሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለ እኩዮቹ ያበሽቁት እንደነበረ የቀድሞ ጓደኞች እና የቤተሰብ አባላት ተናግረዋል።

ከራሞስ ጋር 8ኛ ክፍል አብሮ የተማረ የክፍል ጓደኛው፣ ራሞስ ኮልታፋ በመሆኑ ተማሪዎች አብዝተው ያበሽቁት እንደነበረ ለዋሽንግተን ፖስት ተናግሯል።

የ41 ዓመቱ የራሞስ ጎረቤት ደግሞ ለሲቢኤስ ሲናገር ራሞስ የወላጅ ፍቅር ሳይገኝ ነው ያደረገው ብሏል። "ከባድ ሕይወት ነው ያሳለፈው እናቱ የዕጽ ሱሰኛ ናት፣ ምንም አይነት ፍቅር አሳይታው አታውቅም" ብሏል።

ይህ ጎረቤት እንደሚለው ከሆነ ራሞስ የ14 ወይም የ15 ዓመት ጎረምሳ ከሆነ በኋላ ባህሪው መቀያየሩን እና ከራሞስ ጋር ንግግር ማድረግ ከባድ እንደሆነ ይናገራል።