የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያሸነፈው የፈጠራ ሥራ

ሐብታሙ አባፎጊ

የፎቶው ባለመብት, Habtamu Abafogi

ሐብታሙ አባፎጊ ይባላል። በጅማ ዩኒቨርስቲ የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ መምህር ሲሆን፣ የሲምቦና አፍሪካ ሔልዝ ኬር መስራች እና ኃላፊ ነው።

ሐብታሙ ከመምህርነቱ ባሻገር ስሙን የተከለው በጤና ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ፈጠራ ነው።

በእነዚህ የፈጠራ ሥራዎቹ የተነሳም የተለያዩ ሽልማቶችን ተቀብሏል።

ከሐብታሙ የፈጠራ ስራዎች መካከል አንዱ የሕጻናትን የሰውነት ሙቀት መጠን በተፈለገው ደረጃ ላይ በማስተካከል በሙቀት ከፍ ማለት አማካኝነት ከሚከሰቱ ሕመም ሀይፖተርሚያ (Hypothermia) እንዳይጠቁ የሚረዳ መሳርያ ነው።

ሀይፖተርሚያ ሰውነታችን ከሚያመነጨው ሙቀት በላይ ሙቀት በፍጥነት ሲቀንስ እና ጤናችን አደጋ ላይ ሲወድቅ ይከሰታል።

የዓለም ጤና ድርጅት የአንድ ጤነኛ ሰው አማክኝ የሰውነት ሙቀት፣ 36.5-37.5 ሴንቲ ግሬድ መሆን አለበት ይላል።

ከዚህ በታች የሆነ ሙቀት ሐይፖተርሚያ በመባል ይታወቃል።

የሰውነት ሙቀት መጠን በከፍተኛ መጠን ከቀነሰ የነርቭ ስርዓታችንን እና ሌሎች የአካል ክፍሎቻችን በአግባቡ ስራቸውን መከወን አይችሉም። ይህም ሁኔታ ተገቢውን ሕክምና ካላገኘ ለሞት እንደሚዳርግ ሐብታሙ ይናገራል።

ሐብታሙ የሰራው ይህን የፈጠራ ውጤት 'ኢንፋንት ራዲያንት ዋርመርስ' በመባል ይታወቃል።

ሐብታሙ የሰራው የፈጠራ ስራ

የፎቶው ባለመብት, Habtamu Abafogi

መሳርያው ሁለገብ ጥቅም የሚሰጥ መሳርያ መሆኑን ይናገራል።

በዚሁ በሀይፖተርሚያ ምክንያት በዓመት ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ሕጻናት እንደሚሞቱ ሐብታሙ ይናገራል።

ዩኒሴፍን በመጥቀስም በኢትዮጵያም በዚሁ በሽታ በቀን ወደ 240 ሕጻናት ሕይወታቸው እንደሚያልፍ በማንሳት፣ ይህንኑ ችግር ለመፍታት 'ኢንፋንት ራዲያንት ዋርመር' ሲል የሰየመውን መሳርያ ለመስራት መነሳሳቱን ይናገራል።

"እኛ የሰራነው ማሽን የሕጻናትን ሞት ከማስቀረቱም በተጨማሪ የማህበረሰቡን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለን እናምናለን" ሲል ይናገራል።

ሐብታሙ ይህንን ሲያብራራ አንዱን መሳርያ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት፣ ኢትዮጵያ ወደ አምስት ሺህ ዶላር እንደምታወጣ ይገልጻል። "ይህ ማሽን በአገር ውስጥ ከተሰራ ግን ዋጋው በሶስት እጥፍ ይቀንሳል።" ሲልም ያክላል።

በተጨማሪም ይላል ሐብታሙ ይህ ማሽን ሙሉ የኤሌክትሮሜካኒካል ስራው ዲዛይኑ በአገር ውስጥ የተሰራ መሳርያ ነው።

ሐብታሙ የሰራው የፈጠራ ስራ

የፎቶው ባለመብት, Habtamu Abafogi

ለፈጠራው መነሻ የሆኑ ሰበቦች

ሐብታሙ ተማሪ በነበርበት ወቅት አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለስራ ላይ ስልጠና ሄዶ ያየውን ያስታውሳል።

በቆይታው ወቅት ሕይወትን ለማትረፍ ሕክምና ላይ የሚውሉ የተለያዩ ማሽኖች በተደጋጋሚ ሲበላሹ ተመለከተ።

"በተደጋጋሚ እንጠግናለን። ተመልሶ ይበላሻል፤ እኔም ይህንን ከተመለከትኩ በኋላ ለምንድን ነው ብዙ ጊዜ በጥገና ላይ ጊዜዬን የማሳልፈው። ለምን በራሴ አዲስ ለሕክማና ቴክኖሎጂ የሚውል መሳርያ አልሰራም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። ይህ ሃሳብ ነው ወደ ዚህ የፈጠራ ስራ ያስገባኝ " ይላል።

በተጨማሪም በዩኒቨርስቲው የሚገኙ አንዳንድ አስተማሪዎች ለሐብታሙ የፈጠራ ስራ ብርታት እንደሆኑለት ይናገራል።

ይኹን እንጂ "በመጀመርያ ደረጃ ያንተን ሃሳብ እምብዛም የሚቀበል ሰው አታገኝም፤ በአካባቢዎች ከሚገኙ እቃዎች በማሰባሰብ የፈጠራ ስራን እሰራለሁ ስል አንዳንድ ሰዎች እምብዛ ፋይዳ ያለው መሳርያ አልመሰላቸውም ነበር።"

እኔ ራሴም ብሆን ይላል ሐብታሙ "አሁን ያወጣሁበትን ገንዘብ ያህል እንደሚፈጅ እና በአገር ውስጥም ይህንን መሳርያ ለመጠቀም እምብዛም መነሳሳት እንደሌለ አስቀድሜ ባውቅ ኖሮ ወደዚህ የፈጠራ ሥራ አልገባም ነበር" በማለት በሂደቱ ውስጥ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ያስታውሳል።

መሳርያውን ለመስራት የሚያስፈልጉትን መሳርያዎች ከጅማዋ መርካቶ እስከ አዲስ አበባዋ መርካቶ ምን አለሽ ተራ፣ ከኬንያ እስከ ጆሃንስበርግ አፈላልጎ 'ፕሮቶታይፑ'ን ለመስራት መቻሉን ያናገራል።

በአሁኑ ሰዓት አስፈላጊውን የቁጥጥር መስፈርት በማለፍ ወደ ምርት ስራ መግባት ብቻ እንደቀረው በመግለጽም የሚያበረታቱ ነገሮች እንዳሉ ገልጿል።

የጤና መሳርያዎችን ጥገና ከአዲስ አበባ ውጪም ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን የሚያስረዳው ሐብታሙ፣ "የኛ እቅድ ግን በ130 ኪሜ ራዲየስ የጤና መሳርያዎች ጥገና ማዕከል እንዲኖር ማድረግ ነው" ይላል።

በሌላ በኩል ይህ ማሽን ለጥናት እና ምርምር ሊውል የሚችል የመረጃ ዳታ ቤዝ ያለው መሆኑን እና ችግር በሚያጋጠምበት ጊዜም ማስጠንቀቅያ ስለሚሰጥ እነዚህ ሁኔታዎች ማሽኑን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል መሆናቸውን ይጠቀሳል።

በአጠቃላይ ይህ የፈጠራ ውጤት የሕጻናትን ሞት በመቀነስ፣ የውጪ ምንዛሬን በማዳን፣ የስራ እድልን በመፍጠር እንዲሁም የፈጠራ ስራዎችን በማበረታታት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብሎ እንደሚያምን ይናገራል።

ሽልማቶችን ያገኘው ፈጠራ

ይህ ፕሮጀክት ከአራት ዓመት በፊት ታላቅ የፈጠራ ስራ ውድድር ኢትዮጵያ 'Grand challange Ethiopia' ላይ ቀርቦ በማሽነፍ ዳጎስ ያለ ብር ለመሸለም በቅቷል።

የማሽኑ የኢንጂነርኒግ ስራ ከሁለት ዓመት በፊት አልቆ የሚያስፈልጉት የወረቀት ስራዎች ቢጠናቀቁም በተቆጣጣሪ ተቋማት እና በፋይናንስ ምክንያት በሚፈለገው መጠን ወደ ማህበረሰቡ ሳይደረስ መቆየቱን ያስረዳል።

"አሁን ግን ጉዳዩን የሚመለከታቸው ሁሉ አስፈላጊውን ትኩረት እየሰጡን ስለሆነ ይህንን ማሽን ወደ መስራት ተመልሰን ለታካሚዎች አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጥ እናደርጋለን" በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሐብታሙ የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተበት እና በተስፋፋበት ወቅት 'ዩቪ አልትራቫዮሌንት ስትራላይዜሽን' (uv ultraviolent sterilization) የተሰኘ ማሽን በመስራት በኢትዮጵያ ከ50 በላይ ከተሞች ገበያ ላይ ማቅረቡን ይገልጻል።

በዚህም የስራ እድል መፍጠር መቻሉን እና የጤና አገልግሎት በማሻል ውስጥ አስተዋጽኦ ማድረጉን እና ማሽኖቹም እክል በሚያጋጥማቸው ወቅት በፍጥነት ጥገና ማድረግ መቻሉን ይናገራል።

ይህ የፈጠራ ስራ ከዚህ በፊትም 'ግራንድ ካናዳን ቻሌንጅ' በሚባል ውድድር እና በአገር ውስጥ ደግሞ 'ግራንድ ኢትዮጵያ ቻሌንጅ' ከመቅረቡም በተጨማሪ በአገር ውስጥና ከውጪ አገር በአምስት የተለያዩ ውድድሮች ላይ ማሸነፉን ሐብታሙ ተናግሯል።

በመጨረሻም በዚህ የፈጠራ ስራ በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ጤና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች እውቅና ማግኘቱን ይናገራል።