የወር አበባ እረፍት ዘግይቶም ቢሆን ተቀባይነት እያገኘ ይሆን?

ጥቂት የማይባሉ ትልልቅ ተቋማት ሰራተኞች የወር አበባቸውን በሚያዩበት ወቅት እረፍት እንዲወጡ ለማድረግ አንዳንድ ጥረቶችን ጀምረዋል።

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ አዲስ ስራ የጀመረችው የ28 ዓመቷ ጄሲ ኒው ዮርክ ውስጥ በስራ ቦታ ላይ ራሷን ስታ ወደቀች።

ያን ቀን የወር አበባዋ እንደሚጀምርና ህመም ሊሰማት እንደሚችል ታውቅ ነበር። ነገር ግን መጨረስ የነበረባት ስራ ስለነበረ ነው ወደ ቢሮ የገባችው።

በዚህ ምክንያት አሞኛል እንኳን ብላ ማስፈቀድ አልፈለገችም። ''የወር አበባ እንደ ሕመም የሚቆጠር አይመስለኝም ነበር'' ትላለች።

ያን ቀን ጄሲ ሙሉ ሰውነቷ ሕመም ይሰማት ነበር፤ ሆዷ አካባቢ ከፍተኛ ሕመም እንዲሁም ጀርባዋም አካባቢ ያማት ነበር። ህመም ማስታገሻ ወስዳ ስራዋን ለመቀጠል ወሰነች። ነገር ግን ከ15 ደቂቃ በኋላ መቋቋም የማትችለው ህመም እንዲሁም የማዞር ስሜት ተሰማት።

''ሁሉም ነገር ብዥ አለብኝ። ትንፋሼ መቆራረጥና መክበድ ጀመረ። በጣም የመድከም ስሜት ውስጥ ነበርኩኝ። እራሴንም ሳትኩኝ'' ትላለች።

ጄሲ እራሷን ስትስት ባልደረቦቿ ተረባርበው ሶፋ ላይ አስተኟት። የቢሮው የጤና ባለሙያ መጥቶ ከተመለከታት በኋላ ወደ ሆስፒታል እንድትሄድ ተደረገ።

ጄሲ ግን ወደ ሆስፒታል መሄድ አልፈለገችም ነበር። ቤቷ ሄዳ አረፍ ማለትና እራሷን መንከባከብ ነበር የፈለገችው። ''የቀጠረኝ ድርጅት ለወር አበባ የሚሆን መመሪያ ቢኖረው ደስተኛ ነኝ። ሌላው ቀርቶ ለአንድ ቀን እንኳን ቢሆን ቤቴ ማረፍ እችል ነበር'' ትላለች።

ከአጠቃላይ የዓለማችን ሕዝብ 3.9 ቢሊዮኑ ሴቶች እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። በኢትዮጵያም የሴቶች ቁጥር ከወንዶች የሚበልጥ መሆኑን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ ያሳያል።

በሠራተኛው ኃይል ውስጥም የሴቶች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። የዓለም ባንክ ከዓመታት በፊት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በመላው ኢትዮጵያ ካለው ሠራተኛ ኃይል ውስጥ 46.5 በመቶውን የያዙት ሴቶች ናቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ የተመሰረተው የሴታዊት ንቅናቄ ሴቶች በየወሩ የሚያጋጥማቸውን ከወር አበባ ጋር የተያያዘ ሕመም ከግምት ውስጥ የሚከት እረፍት እንዲሰጥ ለማድረግ ከአጋር ተቋማት ጋር በመሆን ዘመቻዎችን ማካሄድ ከጀመረ ቆይቷል።

ሴታዊት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚባል ደረጃ ሴት ሠራተኞችን የያዘ ተቋም ሲሆን በጉዳዩ ላይ ቅስቀሳ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለተቋሙ ሠራተኞች ይህንን የወር አበባ እረፍት መስጠት ጀምሯል።

መሰል አሰራር በአብዛኛዎቹ ድርጀቶች ውስጥ የለም። ነገር ግን ከነጭራሹ የለም ማለት አይቻልም። የወር አበባ እረፍት ይባላል። ሴት ሰራተኞች የወር አበባቸውን ሲያዩ አልያም ምልክቶቹን ሲያስተውሉና ሕመም ሲሰማቸው ከቤታቸው መስራት አልያም ደመወዝ የሚከፈልበት እረፍት እንዲወስዱ ይደረጋል። በዚህም ልክ እንደ ዓመታዊና የሕመም እረፍት ይቆጠራል ማለት ነው።

ባለፉት መቶ ዓመታት ዓለማችን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ መስማማት ሳትችል ቆይታለች። ነገር ግን በርካታ ስራዎችም ሲሰሩ ቆይተዋል። የቀድሞዋ የሶቪየት ሕብረት 1922 ላይ ተመሳሳይ ሕግ አስተዋውቃ የነበረ ሲሆን ጃፓንም እንዲሁ 1947 ላይ ተመሳሳይ መመሪያ ይፋ አድርጋ ነበር።

ነገር ግን አሁንም ድረስ እንደ አሜሪካ ባሉ ባደጉት አገራት ጭምር እንኳን ሴቶች ወር አበባቸውን ሲያዩ እረፍት እንዲወጡ አልያም ከቤታቸው እንዲሰሩ የሚያደርጉ ሕጎች እምብዛም አይስተዋሉም። በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ የሴቶች መብት ላይ የሚሰሩ ተቋማት፣ ግለሰቦችና እንቅስቃሴዎች በመላው ዓለም የሚገኙ ድርጅቶች መሰል ህጎችን ተግባራዊ አንዲያደርጉ እየወተወቱ ይገኛሉ።

መሰል ህጎች በስፋት ቢተዋወቁ የወር አበባቸውን የሚያዩ ሴቶች ሌላው ቢቀር ከቤታቸው ሆነው ህመማቸውን ስለማስታገስና ስለማገገም ማሰብ ይችላሉ። በስራቸውም ቢሆን ውጤታማ የሚሆኑት መብታቸው ሲከበርላቸውና ጤናቸው ሲጠበቅ ብቻ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ሴቶች የወር አበባ እረፍት እንዲወስዱ የሚጠይቁ እንቅስቃሴዎች ተቃውሞም ይገጥማቸዋል። አንዳንዶች ሴቶች ያልተገባ ጥቅም እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ሲሉ አንዳንዶች ደግሞ የወር አበባ እረፍት የሚወስዱት ሴቶች ላልተገባ መገለልና መድሎ ያጋልጣቸዋል በማለት ይከራከራሉ።

የወር አበባን ተከትሎ የሚመጡ ህመሞችና ምልክቶች ከሰው ሰው ይለያያሉ። አንዳንዶች ምንም ትዝ ሳይላቸው ሳምንቱን ሲያሳልፉ ሌሎች ደግሞ ከባድ ሕመም ውስጥ ሆነው ቀናቱ እስከሚያልፉ ይጠብቃሉ። ከተለመዱት ሕመሞችና ምልክቶች መካከል የሆድ ሕመም፣ የራስ ምታት፣ የጀርባ ሕመምና ድካም ዋነኞቹ ናቸው።

በኔዘርላንዱ ራድባውንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኘው የሕክምና ማዕከል ከ43 ሺህ በላይ ሴቶች የተሰበሰበው መረጃ እንደሚያሳየው፤ 85 በመቶው በወር አበባ ወቅት ከፍተኛ ሕመም ያለው ቁርጠት ያጋጥማቸዋል። እንዲሁም 77 በመቶው የስሜት መረበሽ ውስጥ ሲገቡ 71 በመቶው ዝለት እና ድካም ያጋጥማቸዋል።

በርካታ ሴቶች ታዲያ እነዚህን ሕመሞች ተቋቁመው በስራ ገበታቸው ላይ መገኘት ግዴታቸው ነው። እነሱም ቅሬታቸውን ሲያሰሙ አይስተዋልም።

''ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ ሴቶች ስለ ወር አበባቸው ከአለቆቻቸውና ከወንድ የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ለማውራት ፈቃደኛ ስላልሆኑ ነው። እሱም ደግሞ የራሱ የሆነ ምክንያት አለው። ዋነኛው ምክንያት አብዛኛው ማህበረሰብ በይፋ ስለ ወር አበባ ለማውራት ፈቃደኛ ስላልሆነ ነው። በተለይ ደግሞ ወንዶች'' ትላለች በሳውዝ አውስትራሊያ አደሌይድ ተቋም የሕግ መምክሯ ጋብሪኤል ጎልዲንግ።

በአውሮፓውያኑ 2021 አውስትራሊያ ውስጥ በተሰራ አንድ ጥናት ከተሳተፉ 700 ሴቶች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ከሚቀርቧቸው ሴት ጓደኞቻቸው በስተቀር ከወንድ ባልደረቦቻቸውም ሆነ ከአለቆቻቸው ጋር ስለ ወር አበባቸው ማውራት ጥሩ ስሜት አይሰጣቸውም።

ከዚህ በፊት ስለነበራቸው ልምድ የተጠየቁት እነዚሁ ሴቶች ከመካከላቸው 80 በመቶ የሚሆኑት መሰል ነገሮችን በስራ አካባቢ በማውራታቸው ምክንያት ከሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት መቀየሩን ገልጸዋል።

በተለያዩ አገራት የተለያየ አይነት የወር አበባ ፈቃዶችን በሕግ ደረጃ ያስተዋወቁ አገራት ቁጥር ከፍ እያለ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ አፍሪካዊቷ ዛምቢያ ትገኝበታለች። በዛምቢያ ሴቶች በወር ውስጥ አንድ ቀን ዕረፍት ይሰጣቸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈር ቀዳጅ የምትባለው ጃፓን ስትሆን የወር አበባ ፈቃድ መስጠት ከጀመረች 71 ዓመታት ተቆጥረዋል። ደቡብ ኮሪያም ይህንን መተግበር ከጀመረች ከ60 ዓመታት በላይ ሆኗል።

ደቡብ ኮሪያ ሴት ሠራተኞች በወር ሁለት ቀን የወር አበባ ፈቃድ ከማግኘት አልፎም ይህንን ፈቃዳቸውን ካልተጠቀሙበት በገንዘብ ተሰልቶ እንዲከፈላቸው ታደርጋለች። ታይዋን ደግሞ ሦስት የወር አበባ ፈቃድ ቀናትን ትሰጣለች።

የወር አበባ ፈቃድ በቻይና እና በሕንድም ከፍተኛ ተቀባይነትን እያገኘ መጥቷል። የተወሰኑ የቻይና ግዛቶች ፈቃዱን አጽድቀዋል። አስገዳጅ ሕግ በሌለባቸው አገራት ድርጅቶች በውስጥ ፖሊሲያቸው ሴቶች በየወሩ የሚያጋጥማቸውን ይህንን ሕመም ያማከለ ፈቃድ ማስተዋወቅ ጀምረዋል።

በኢትዮጵያም ይህንን ሃሳብ ለማስተዋወቅ ሦስት ሴቶች ላይ የሚሰሩ ተቋማት ዘመቻዎችን ማካሄድ ጀምረዋል። ሴታዊት፣ ኖብል ካፕ እና አዲስ ፓወር ሐውስ ጉዳዩ አጀንዳ እንዲሆን እና በአሰሪ እና ሠራተኛ ሕጉ ውስጥም እንዲካተት ለማስቻል አቅደው እየሰሩ ነው።

ሴቶች የወር አበባቸውን ሲያዩ እረፍት እንዲያገኙ የሚያደርጉ ሕጎች ቀስ እያሉም ቢሆን በተለያዩ አገራት እየተሞከሩ ነው። መሰል ሕጎችንና ጥቅማትቅሞችን አሁን ላይ በስፋት ተግባራዊ እያደረገች የምትገኝ አገር አውስትራሊያ ነች።

የኮሮናቫይረስ ወርርሽኝን ተከትሎ ሚሊየኖች ከቤታቸው መስራት መጀራቸውን ተከትሎ ውጤታማነት ቀንሷል ይባላል።

የተለያዩ የአውስትራሊያ ድርጅቶችም ሰራተⶉቻቸው ወደ ቢሮ ከተመለሱ በኋላ ውጤታማነታቸው እንዲጨምርና በታማኝነት ስራቸውን እንዲሰሩ ለማድረግ የተለያዩ አማራጮችን እየፈለጉ ነው።

ከነዚህ አማራጮች መካከል ደግሞ ሴት ሰራተኞቻቸው የወር አበባ እረፍት እንዲያገኙ በማድረግ ደስተኛ እንዲሆኑና ውጤታማነታቸው እንዲጨምር ማድረግ ነው።