ከአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሾልኮ የወጣ ሰነድ የፅንስ ማቋረጥ ሕግ ሊሻር እንደሚችል አመለከተ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፅንስ የማቋረጥን ሕጋዊ መብት ሊሻር እንደሚችል የሚጠቁም ሾልኮ የወጣ ረቂቅ ሰነድ መነጋገሪያ ሆኗል።
ዳኛ ሳሙዔል አሊቶ ሾልኮ ወጣ በተባለው ሰነድ ላይ ፅንስን ሟቋረጥ የሚፈቅደውን የ1973ቱን 'ሮይ ቨርሰስ ዌድ' የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ውሳኔ "ከፍተኛ ስህተት ነው" ማለታቸውን ፖለቲኮ ዘግቧል።
የአሜሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይህንን ውሳኔ ከቀለበሰ በ22 የአሜሪካ ግዛቶች ፅንስ ማቋረጥን ሕገ ወጥ ሊያደርግ ይችላል።
የዳኛ ሳሙኤል አሊቶ አስተያየት በአብላጫ ድምጽ ውሳኔውን ማስቀልበስ ከቻለ በአገሪቱ ያለው ፅንስ የማቋረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብት ተሽሮ ግዛቶች አሰራሩን ሙሉ በሙሉ እንዲያግዱ መንገድ ይከፍታል ወይም በላዩ ላይ ተጨማሪ ገደቦችን መጣል ያስችላቸዋል።
ፍርድ ቤቱ እስከ ሐምሌ ወር መጀመሪያ ድረስ በጉዳዩ ላይ ብይን ይሰጣሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ሮይ ቨርስስ ዌድ የተሰኘው የ1973 ሕግ በአሜሪካ ላሉ ነፍሰ ጡር ሴቶች በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት እርግዝና ውስጥ ፅንስ የማቋረጥ ፍጹም መብት እና በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ የተወሰኑ መብቶችን ሰጥቷቸዋል ።
የ1973 ሕግ ወደ ፍርድ ቤት እንዲመጣ ምክንያት የሆነው የሚሲሲፒ ግዛት ከ15 ሳምንታት በኋላ ፅንስ ማቋረጥ ላይ እገዳ በመጣሏ ሲሆን ይህንንም ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ታኅሳስ ወር ላይ ተመልክቶታል።
በአሜሪካ ወደ ሪፐብሊካኖቹ ባዘነበለው ሥርዓትና የስነ ተዋልዶ መብቶች ፈተና ላይ ባሉበት ማግሥትም ነው ይህ ፅንስ ማቋረጥን የሚፈቅደው 'ሮይ ቨርሰስ ዌድ' አደጋ ላይ መሆኑ የተነገረው።
ፅንስን ማቋረጥ ውሳኔን ሊሽር ይችላል የተባለው ይህ ሰነድ በዲሞክራቶች ዘንድ ተቃውሞን አስነስቷል። በተጨማሪም ሰኞ ምሽት ፅንስን ማቋረጥ የሚደግፉና የሚቃወሙ ሰልፈኞች በጠቅላይ ፍርድ ቤት ድምጻቸውን በተለያየ መልኩ አሰምተዋል።
ሰኞ ምሽት አፈትልኮ ወጣ በተባለው ሰነድ ላይ ጠቅላይ ፍርድቤቱም ሆነ ዋይት ሃውስ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ሾልኮ የወጣው ረቂቅ ሰነድ "'ሮይ ቨርሰስ ዌድ" የተሰኘው ውሳኔ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከፍተኛ ስህተት ነበር ሲል ያትታል።
አክሎም ሕገ መንግሥቱን አክብረን የፅንስ ማቋረጥን ጉዳይ ሕዝብ ለመረጣቸው ተወካዮች ለመመለስ ጊዜው አሁን ነው ብሏል።
እንደ ዘገባው ከሆነ የነፍሰ ጡር ሴትን ነጻነት ለመጠበቅ የወጣው "'ሮይ ቨርሰስ ዌድ" ምክንያት በተለየ መልኩ ደካማ ነበር እና መዘዞችንም አስከትሏል" ሲሉ ዳኛ ኦሊቶ ጽፈዋል።
አክለውም "ውሳኔው ብሔራዊ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ክርክርና መከፋፈልን በአገሪቱ አስፍኗል" በማለት ፖለቲኮ ዳኛ ኦሊቶን ዋቢ አድርጎ አስፍሯል።
ወግ አጥባቂው በአስተያየታቸው "ልንዘለው የማንችለው ድምዳሜ ጽንስ የማቋረጥ መብት በአገሪቷ ታሪክና ወግ ሥር የሰደደ አይደለም የሚለው ነው" ብለዋል።
የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ እና የምክርቤቱ አብላጫ መሪ ቻክ ሹመርም አፈትልኮ ወጣ በተባለው አስተያየት ላይ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሁለቱ ዲሞክራቶች በመግለጫቸው፣ ዘገባው ትክክል ከሆነ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛውን የመብት ገደብ ለመፈፀም ተዘጋጅቷል ማለት ነው ብለዋል።
በሪፐብሊካን የተሾሙት ዳኞች ውሳኔም በዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ከተፈፀሙት እጅግ የከፉ እና በጣም ጎጂ ውሳኔዎች አንዱ ወደሆነው አጸያፊው ተግባር እያመራ ነው" ሲልም መግለጫው አክሏል።
ይህንን ተከትሎ ተቃዋሚዎች በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመሰባሰብ ሾልኮ በወጣው ሰነድ ላይ ያላቸውን ቁጣ ገልጸዋል።
ተቃዋሚዎቹ " ከሰውነታችን ላይ እጃችሁን አንሱ"፣ "የሴቶች መብት ሰብዓዊ መብት ነው"፣ "አካሌ ምርጫዬ ነው" የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ወጥተዋል።
የፀረ ፅንስ ማቋረጥ ተሟጋቾች በበኩላቸው "ሮይ ቨርሰስ ዌድ" መነሳት አለበት ሲሉ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
በአገሪቷ ካሉ ፅንስን ማቋረጥን ከሚቃወሙ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነውና ናሽናል ራይት ቱ ላይፍ የተባለው ድርጅት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠቱ በፊት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ይፋዊ አስተያየት እንደሚጠብቅ ገልጿል።
እንደ ፖለቲኮ ከሆነ ሾልኮ የወጣው ሰነድ "የመጀመሪያ ረቂቅ" ተደርጎ የተጠቀሰ ሲሆን የካቲት ወር ላይ ተሰራጭቷል። በማርቀቁ ሂደቱ ወቅትም የፍትህ ዳኞቹ ድምጽ የተለያየ እንደነበርም ታውቋል።
ጠቅላይ ፍርድቤቱ በእንዲህ ዓይነት ጉዳዩ ላይ ብይን ሲሰጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። እአአ በ1992 ዳኛ አንቶኒ ኬኔዲ በመጨረሻው ሰዓት ሃሳባቸውን ለውጠው ወሳኝ የነበረውን አምስተኛውን ድምጽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው "ሮይ ቨርሰስ ዌድን" ሕግ ለመጣል ብዙኃኑን ተቀላቅለዋል።












