አማዞን በአሜሪካ ለሚገኙ ሠራተኞቹ ፅንስ ማቋረጥን ጨምሮ ለሌሎች ህክምናዎች የጉዞ ወጪዎችን ሊሸፍን ነው

የአማዞን ሠራተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አማዞን ይፋ ያደረገው ይህ አዲስ አሰራር ከባለፈው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ ወደ ኋላ ሄዶ ይተገበራል ተብሏል።

ግዙፉ የኦንላይን መገበያያ አማዞን በአሜሪካ የሚገኙ ሠራተኞቹ በምርጫ የሚደረግ ፅንስ ማቋረጥን ጨምሮ የተለያዩ ህክምናዎችን ለማድረግ የሚያደርጉትን የጉዞ ወጪ እሸፍንላቸዋለሁ አለ።

ድርጅቱ በቅርበት የማይገኙ ህክምናዎችን ለሚያደርጉ ሠራተኞች እስከ 4ሺህ ዶላር ድረስ ሊከፍልላቸው ማቀዱን ለሠራተኞቹ ባስተላለፈው መልዕክት ገልጿል።

ከአማዞን በተጨማሪ የተለያዩ ክባንያዎች የኢንሹራንስ መብት ያላቸው ሰዎች ኢንሹራንሱን ተጠቅመው ፅንስ ማቋረጥ እንዲችሉ እየፈቀዱ ነው።

አማዞን ይፋ ያደረገው ይህ አዲስ አሰራር ከባለፈው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ ወደኋላ ሄዶ ይተገበራል ተብሏል።

የዚህ አሰራር ተጠቃሚ የሚሆኑ ሠራተኞች የሚፈልጉት ህክምና ከመኖሪያ ቤታቸው በ161 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ አለመኖሩን ወይም ህክምናው በበይነ መረብ የሚሰጥ አለመሆኑ መረጋገጥ አለበት።

አማዞን ለሠራተኞቹ ይፋ ያደረገው ይህ ጥቅም ከፍተኛ ክብደት ለመቀነስ የሚደረግ ህክምና፣ የካንሰር፣ የአዕምሮ ህመም እና ከፅንስ ጋር የተያያዙ ህክምናዎችን እንደሚያካትት የአማዞን ቃል አቀባይ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አማዞን በአሜሪካ ትልቅ ቀጣሪ ከሚባሉ የግል ኩባንያዎች ውስጥ የሚመደብ ሲሆን ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት።

አዲሱ ጤናን የተመለከተው አሰራር በቢሮዎች እና መጋዘኖች ለሚሰሩ ሁሉም ሰራተኞች ተግባራዊ የሚደረግ ነው።

ኩባንያው አስቸኳይ የሕይወት አድን ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ሠራተኞቹ እስከ 10 ሺህ ዶላር እንደሚያቀርብም ተሰምቷል።

ይህ የአማዞን የሠራተኞች ጥቅማ ጥቅም ዕቅድ በርካታ የሪፐብሊካን ግዛቶች ፅንስ ማቋረጥን የሚከለክል ሕግ እያወጡ ባለበት ሰዓት ይፋ የሆነ ሲሆን አማዞን ግን ፅንስ ማስወረድን በተለየ ሁኔታ ለመፍቀድ ይፋ ያደረገው አሰራር አይደለም።