በቡና እና በጨው ሥዕሎቿን የምትሠራው ገሊላ ረዳ

በአባቷ አቶ ረዳ ቤት ጥበብ በገሊላ ብቻ አይደለችም ያደረችው፤ አሁን በሕይወት የሌለ ታላቅ ወንድሟም ጎበዝ ሠዓሊ ነበረ።

ወንድሟ በሚሥልበት ግዜ ስትመለከት የነበረችው ገሊላም የጥበብ ስሜት በሕፃን አእምሮዋ አድሮ ገና የስድስት ዓመት ልጅ ሳለች ብሩሽ ጨበጠች።

ታላቅ ወንድሟ የሣላቸውን ሥዕሎች በግድግዳ እና በደብተሯ ላይ ደግማ በመሣል ነው ሥዕልን አሃዱ ብላ የጀመረችው።

ወላጅ እናቷ የምትሰፋቸው ስፌቶች እና ጥለቶችም በገሊላ የጥበብ መንገድ ላይ ጫና ማሳደራቸውን ትናገራለች።

ገሊላ ምንም እንኳን ከልጅነቷ ጀምሮ ከብሩሽ ጋር የማትለያይ የነበረች ብትሆንም፣ በቤት ውስጥም ወላጅ እናቷን እያገዘች ሥዕል ትሥል እንደነበረች ታስታውሳለች።

"ቤታችን ለብዙ ዓመታት ምግብ ቤት ነበረን። . . .የ12 ዓመት ልጅ ሆኜ ለደምበኞች ምግብ እሰራ እና እንጀራ እጋግር ነበር፤ ይህን እየሠራሁም በጎን ሥዕል እሥል ነበር።"

በልጅነቷ ለእርካታዋ ብላ ትሥለው የነበረው እና ቀልብዋን የገዛው ሥዕል፣ ካደገች በኋላ አድጎ የሙሉ ጊዜ ሥራዋ ሆነ።

እንደ ገሊላ ገለጻ፣ አእምሮዋ ያረገዛቸውን ጥበባዊ ሐሳቦች ወደ ሥዕል ለመቀየር 'አክለሪክ' ቀለም፣ ቡና እና ጨው ትጠቀማለች።

ገሊላ በኖርዌይ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ብታጠናም ሥዕል ግን ያስተማረችው ራሷን በራሷ ነው።

"ብዙ ግዜ የተሰማኝን፣ የማየው እና መነሳሳት የሚፈጥርብኝ ነገር እሥላለሁ" የምትለው ገሊላ፣ አብዛኛውን ግዜ የሴቶች ውበት እና ጥንካሬ በሥዕሎቿ ተወክለው ይታያሉ።

ባሕር የተሻገረ የሥዕል ዐውደ ርዕይ

አሁን ስዊድን የምትኖረው ገሊላ ረዳ፣ በተለይም ከ2011 የአውሮጳውያን አቆጣጠር ጀምሮ በተለያዩ የዓለም አገራት በመዞር ዓውደ ርዕይ (solo exhibition ) በማዘጋጀት ስራዎችዋን ለጥበብ አፍቃርያን እያስተዋወቀች ነው።

ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ አሜሪካ እና ቤልጂዬም ደግሞ ገሊላ በታዳሚዎች ፊት በቀለም እና በቡና ሥዕሎቿን በመሣል ትርዒቷን ያቀረበችባቸው አገራት ናቸው።

"በሥራዎቼ በተለያዩ አገራት ብዙ አድናቂዎች አግኝቻለሁ። ከዚህ የሚበልየጥ ሽልማት የለም" ስትል ታክላለች።

ገሊላ በዓለም አቀፍ የቡና ቀን በኖርዌይ ታዋቂ የሆነው የቡና ድርጅት 'ኖሽክ ካፈላይክ' ጋር በመሆን በቡና የምትሥላቸውን ሥራዎቿን ያቀረበች ሲሆን "ትልቅ ዕድል እና ልምድ የፈጠረልኝ ነው። ከዛ በኋላ ከብዙዎች ጋር እንድሠራ ዕድል ከፍቶልኛል" በማለት አጋጣሚውን ትገልጸዋለች።

ከሥዕሎቿ መካከል በቡና የምትሥላቸው በተለየ ሁኔታ በብዙዎች የተወደዱ መሆኑን ትናገራለች።

"ስላልተለመደ እና የተለየ ስለሆነ፣ በዛ ላይ ሰው ቡና ፍቅር ስላለው ይመስለኛል ብዙ ሰዎች በቡና የምሥላቸውን ሥራዎቼን ይወዷቸዋል።"

በቀለም ከሣለቻቸው የሥዕል ሥራዎችዋ መካከል ደግሞ፣ በአንበጣ ወረርሽኝ ግዜ በደቡብ ትግራይ ራያ አንዲት እናት ልጅ አዝላ አንበጣ ስታባርር የሚያሳየው ሥዕል በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት ያስገኘላት ነበር።

በባሕር ማዶ በ2021 ላይ የሣለችው የማልኮም ኤክስ ሥዕልም በብዝዎች ዘንድ ተወዶላታል፤ ከማልኮም ቤተሰቦችም ምስጋና ያገኘችበት የጥበብ ልጇ ነው።

"የማልኮም ኤክስ ልጅ ኢልያሳህ ሻባዝ አባቷን ስለሳልኩት አድኖቆትዋን እና ምስጋናዋን ገልፃልኛለች" ትላለች ገሊላ።

በትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ካጋጠመ ሞት፣ ስደት እና ሰብአዊ ቀውስ ባሻገር ብዙዎች በስቃይ ውስጥ እየኖሩ እንደሆነ የምትገልጸው ገሊላ፣ ለዚሁ ከባድ ሁኔታ 'የትውልዶች ስቃይ' (generational trauma) በሚል ርዕስ አንድ ሥዕል ሠርታለች።

"አብዛኞቹ ሥዕሎቼ ስሜቴን የሚገልጹ ናቸው። በዚህ ዓመት ከሳልኩዋቸው 'generational trauma' የሚለው የበርካታ ሰው ታሪክ ስለሆነ የተወደደ ሥዕል ነው" ትላለች።

እሽቅድድም ከሐሳቦች ብልጭታ ጋር

ገሊላ ወደ አእምሮዋ ብልጭ የሚሉ፣ ጊዜ የማይሰጡ እና በቅፅበት በአንድነት የሚመጡ የሐሳብ ሰልፎችን በፍጥነት ወደ ንድፍ (sketch) ለመቀየር ፀጥ ያለ ቦታ እንደምትመርጥ ታስረዳለች።

"በማትጠብቂው ቦታ ሁነሽም ወደ አእምሮሽ ሐሳብ ሊመጣልሽ ይችላል። ይህንን ሐሳብ ወደ ሥዕል ለመቀየር የራስሽ ፀጥ ያለ ቦታ ያስፈልጋል፤ ሰው እንዲረብሽሽ አልያም የሆነ ነገር እንዲያሰናክልሽ አትፈልጊም። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በምሆንበት ግዜ፣ ወደ አእምሮዬ የሚጣልኝ ሐሳብ ቆይቶ ሊጠፋ ስለሚችል ንድፍ አወጣለሁ" ትላለች።

ገሊላ አንድ ሥዕል ለመጨረስ በግዜ መገደብ እንደማይቻልና እና ዓመታት አልያም ሰዓታት ሊፈጅ እንደሚችል ትገልፃለች።

"አንዳንዴ የሆነ ሐሳባዊ ሥዕል ዓመታት ሊወስድ ይችላል፤ በአንዴ የሚጨረስ ሥዕልም አለ። አንዳንዱ ደግሞ በአንድ ቀን ውስጥ ሊጨረስ ይችላል። በቡና የምሠራቸው ሥዕሎች ግን በሰዓታት ነው የምጨርሳቸው" ትላለች።

ገሊላ እስካሁን ከሣለቻቸው መካከል ለመቀለ ሃምሊን ፌስቱላ ማእከል በእርዳታ መልክ በጨረታ በመሸጥ ከገንዘብ ጋር ያበረከተችው ሥዕል ልዩ ስሜት ይፈጥርባታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የኑሮ ሁኔታ ምክንያት ብዙ ሰዎች ለጥበብ ቅድሚያ አይሰጡትም የምትለው ገሊላ፣ በአሁኑ ግዜ በትግራይ በተከፈተው ጦርነት ምክንያት ብዙዎች ሕይወታቸውን በስቃይ እያሳለፉት ስለሆነ በጥበብ የሚፈወሱበት ማእከል ለመክፈት ታስባለች።

"ባለው ሁኔታ በብዙ መከራ እያለፈ የሚገኝ ሰው ስላለ ከሌሎች ጋር በመተባበር፣ ሰዎች ከአእምሮ ስቃያቸው የሚፈወሱበት፣ ልጆች እና ወጣቶች የሚዝናኑበት የጥበብ ማእከል (art gallery) ለመክፈት እና በዚህ ዘርፍ ላሉ ባለሙያዎች የሥዕል ቁሳቁስ መርዳት እመኛለሁ።"