ኢትዮጵያ ብትቃወምም ተመድ ሩሲያን ከሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አገደ

የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ሩሲያ ጦሯ ዩክሬን ውስጥ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል በሚል ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አገዳት።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሩሲያን ከሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለማገድ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ተቃውመውት ነበር።

ሩሲያ ከምክር ቤቱ እንድትታገድ 93 አባል አገራት ድጋፍ የሰጡ ሲሆን፤ 24 አገራት ሲቃወሙ 58ቱ ደግሞ ድምጽ አልሰጡም።

የሩሲያን ከምክር ቤቱ መታገድ ከተቃወሙ አገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኢራን፣ ቻይና፣ ሶሪያ፣ ቪዬትናም እና ዚምባብዌ ይጠቀሳሉ።

በርካታ ምዕራባውያን አገራት ግን ሩሲያ ከሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እንድትታገድ ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

ጉዳዩን በድምጸ ተዓቅቦ ካለፉት 58 አገራት መካከል ግብጽ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኳታር፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ዩናትድ አረብ ኤሜሬትስ እና ኡጋንዳ ይገኙበታል።

የጠቅላላ ጉባኤውን ውሳኔ ተከትሎ የዩክሬን የውጭ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ "የሰዎችን መብቶች በሚጠብቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የጦር ወንጀለኞች ቦታ የላቸውም" ብለዋል።

የወጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩሲያ ከምክር ቤቱ እንድትታገድ ድምጽ ለሰጡ አባል አገራት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ረቂቅ የውሳኔ ሐሰብ፤ አንድ አባል አገር ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከፈፀመ ጠቅላላ ጉባኤው ከሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባልነት ሊያግደው ይችላል ይላል።

ጠቅላላ ጉባኤው አንድን አገር ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባልነት ለማገድ ሁለት ሶስተኛ ድምጽ ማግኘት ይጠበቅበት ነበር።