ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቱርክ የኻሾግጂ ግድያ የክስ ሂደት እንዲቋረጥ መወሰኗ ቁጣን ቀሰቀሰ
የቱርክ ፍርድ ቤት በጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያ ክስ የቀረበባቸው 26 የሳኡዲ አረቢያ ዜጎች የፍርድ ሂደት እንዲቋረጠ መወሰኑ ቁጣን ቀሰቀሰ።
የፍርድ ቤቱ ዳኛ የተከሳሾቹ ጉዳይ ከቱርክ ወደ ሳኡዲ ይተላለፍ ሲሉ ወስነዋል።
ሳኡዲ አረቢያ በጋዜጠኛው ግድያ የሚፈለጉትን ዜጎቿን ለቱርክ አሳልፋ ከመስጠት ተቆጥባለች።
የኻሾግጂ እጮኛ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ደስተኛ አለመሆኗን እና ይግባኝ እንደምትጠይቅ ተናግራለች።
የዋሽንግተን ፖስት አምደኛ እና የሳኡዲ ንጉሳዊ አስተዳደርን አጥብቆ ይተች የነበረው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ እአአ 2018 ላይ ኢንስታንቡል ወደሚገኘው የሳኡዲ ቆንስላ ከገባ በኋላ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሏል።
ምዕራባውያን እና የቱርክ መንግሥት ለጋዜጠኛው ሞት ተጠያቂው በሳኡዲ መንግሥት የተላኩ ገዳዮች ናቸው ብለዋል።
ኻሾግጂ በተገደለ ወቅት ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን ጋዜጠኛው፤ ከሪያድ በተላከ "ጨካኝ ገዳይ ቡድን ታቅዶበት" ተገድሏል ብለው ነበር።
የአሜሪካ የስለላ ተቋም ሲአይኤ፤ የሳኡዲ ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ጋዜጠኛው ተይዞ ወደ ሳኡዲ እንዲመጣ አልያም እንዲገደል አዘዋል ብሎ ነበር።
ልዑል አልጋ ወራሹ በጋዜጠኛው ግድያ እጄ የለበትም ሲሉ ቆይተዋል።
ከጋዜጠኛው ግድያ በኋላ ከፍተኛ ወቀሳ የደረሰባት ሳኡዲ አረቢያ፤ በግድያው ጥፋተኛ ናቸው ያለቻቸውን እና ስማቸው ያልተጠቀሱ 8 ሰዎችን እአአ 2019 ላይ ጥፋተኛ ብላ ነበር።
ይህ የቱርክ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተሰማው ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾች በሌሉበት የክስ ሂደቱ ሊጓተት ይችላል በሚል ለቱርክ ፍትሕ ሚኒስቴር ያቀረው ምክረ ሃሳብ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ነው ተብሏል።
ዐቃቤ ሕግ በጋዜጠኛው ግድያ ቱርክ ክስ የመሰረተችባቸው ግለሰቦች ጉዳይ እንደሚመረመር ሳኡዲ አረቢያ ቃል ገብታለች ብሏል።
ይሁን እንጂ ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከፍተኛ ነቀፌታ ገጥሞታል። በቱርክ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ኃላፊ ውሳኔው ፖለቲካዊ ነው ብለዋል።
በጋዜጠኛው ግድያ ተፋጠው የነበሩት ቱርክ እና ሳኡዲ በአሁኑ ሰዓት የሻከረ ግንኙነታቸውን ለማደስ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።