በምንጃር እና ፈንታሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተው ምንድን ነው?

ከአዲስ አበባ ሰሜን ምሥራቅ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል በሚዋሰኑበት አካባቢ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ነዋሪዎችና የፀጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት መድረሱን የአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት ገለጹ።

የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞኖች በሚዋሰኑበት አካባቢ ጥቃት መፈጸሙንም የሁለቱም ዞኖች አስተዳዳሪዎች ገልጸው በጥቃቱ የፌደራል ፖሊስ አባላት፣ የአካባቢ ሚሊሻዎችና በነዋሪዎች ላይ ሞትና ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል።

ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ በግልጽ ባይነገርም በሁለቱም አካባቢዎች ያሉ አስተዳዳሪዎች ግን አንዳቸው ከአንዳቸው ተጎራባች ወረዳ የመጡ ታጣቂዎች እንደሆኑ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች ይህንን ከስተት በተመለከተ ባወጡት መግለጫ ላይ ጥቃቱን የፈጸሙት "ጽንፈኛ ኃይሎች" መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህም በማኅበረሰቦች መካከል ግጭትን ለመፍጠር የታቀደ ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊትም በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በይዞታ ይገባኛል ምክንያት አልፎ አልፎ ግጭቶች ያጋጥሙ የነበረ ሲሆን፣ የአሁኑ ጥቃት ግን የፀጥታ ኃይሎች ላይ ያነጣጠረ ነው።

የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች ጥቃት ፈጻሚዎቹን ተከታትሎ በመያዝ ለሕግ ለማቅረብ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ባወጡት መግለጫ አመልክተዋል።

የተከሰተው ምነድን ነው?

ማከሰኞ መጋቢት 20/2014 ዓ.ም በተከሰተው ጥቃት የሰሜን ሸዋ የምንጃር ሸንኮራ እና በምሥራቅ ሸዋ የፈንታሌ ኃላፊዎች እንደሚሉት ታጣቂዎቹ ከሌላኛው አካባቢ እንደመጡና ጉዳት እንዳደረሱ ይናገራሉ።

በአማራ ክልል ባለው የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ቦሰት እንዳሉት ከኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ በሆነዉ አሞራቤት ቀበሌ አውራ ጎዳና መንደር ላይ ታጣቂዎቹ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ዋና አስተዳዳሪው ከአጎራባቹ የኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ መጡ ያሏቸው ጥቃት ፈጻሚዎቹ "የተደራጁ እና የቡድንና በከባድ መሳሪያ የታጠቁ" መሆናቸውን አመልክተው፣ በጥቃቱ የሰው ሕይወት መጥፋቱንና ንብረት መጎዳቱን በወረዳው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ አመልክተዋል።

በአካባቢው ከዚህ ቀደምም የተለያዩ ጥቃቶች ያጋጥሙ እንደነበር የገለጹት አቶ ታደሰ ከቀናት በፊት የተፈጸመው ጥቃት መነሻ በግልጽ እንደማይታወቅ ገልጸው "ምናልባትም ማንነታቸው ያልታወቁ ፀረ ሰላም ኃይሎች አቅደው አካባቢውን በማውደም ነዋሪዎችን ለማፈናቀል አልመው" የፈጸሙት ሊሆን እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

በኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው ከአጎራባቹ የአማራ ክልል አካባቢ የመጣ ታጣቂ ቡድን በዞኑ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ፈጽሞ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

ነገር ግን በቀጣይ ቀናት ጥቃቱን የፈጸመው አካል ማነው? ከየት የመጣነው? የሚለው ይጠራል ያሉት አቶ አባቡ "የብሔር ግጭት መፍጠር የሚፈልጉ በኦሮሚያ እና አማራ ድንበር ላይ የሚንቀሳቀስ የተደራጀ ጽንፈኛ ኃይል ሊሆን ይችላል" የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል።

አስተዳዳሪው ጥቃት ፈጻሚው ቡድን ማንነቱ የማይታወቅ መሆኑን አመልክተው፣ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ እንደሆነና ባለፈው ማክሰኞ በአካባቢው የሚሊሻ አባላት ላይ በፈጸመው ጥቃትም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል ያሏቸው የፀጥታ አባላት ለሥራ ተሰማርተው በቡድን እየተመለሱ ሳለ በተፈጸመባቸው ድንገተኛ ጥቃት ከመካከላቸው 18ቱ መገደላቸውንና 15 ደግሞ መቁሰላቸውን ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የምሥራቅ ሸዋ ፖሊስ አዛዥ ኤቢሳ አሰፋ ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኦቢኤን እንደተናገሩት በጥቃቱ የተገደሉት 26 ሰዎች ናቸው ብለዋል።

የፖሊስ አዛዡ ጥቃቱ ያደረሰው ቡድንን ማንነት ያልገለጹ ሲሆን፣ ነገር ግን "የተደራጀ እና ዘመናዊ ጦር መሳሪያ የታጠቀ ነው" ሲሉ ከተፈጸመው ጥቃት ተነስተው ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

የኦሮሚያ ክልል

ጥቃቱን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ባወጣው መግለጫ ጥቃቱን የፈጸሙት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኘው ምንጃር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መሆናቸውን አመልክቷል።

ክልሉ እንዳለው በምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ቆርኬ/አውራ ጎዳና በሚባለው ልዩ ሥፍራ "በምንጃር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች በጉዞ ላይ በነበሩት የሕዝብ ሚሊሻና የፌዴራል ፖሊስ ላይ" ጥቃት ማድረሳቸውን አስታውቆ ሐዘኑን ገልጿል።

ጥቃቱ "የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ዘላቂ አብሮነትና ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞን ለማደናቀፍ በጽንፈኛ ኃይሎች የተወጠነ የጥፋት ዕቅድ አካል" ነው በማለት፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለሕግ ለማቅረብ እንደሚሰራ የኦሮሚያ ክልል አመልክቷል።

ጨምሮም የኦሮሚያ ክልል ከአማራ ክልል ጋር በመሆን ጥቃቱ በደረሰበት ቦታ ላይ ተገቢውን ክትትል በማድረግ ወንጀለኞችን ህግ ፊት ለማቅረብ በጋራ እየሠራ መሆኑን አመልክቷል።

የአማራ ክልል

ይህንን ጥቃት ተከትሎ የአማራ ክልል ባወጣው መግለጫ ተመሳሳይ ጥቃቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ መፈጸማቸውን አስታውሶ፣ የክልሉ መንግሥት በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በሰውና በንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል።

ጨምሮም "ተስፈኛ ጽንፈኞችና አሸባሪዎች" ያለቸው ኃይሎች በአማራ ክልል ሕዝብ እና በአጎራባች ክልል ሕዝብ መካከል ግጭት ለመፍጠር እንዲሁም የክልሉን ሕዝብ "ማኅበራዊ እረፍት ለመንሳት በክልላችን አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት ለማጫር ተንቀሳቅሰዋል፤ እየተንቀሳቀሱም ይገኛሉ" ይገኛሉ ብሏል።

መግለጫው "ከጽንፈኛና ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ የጥፋት ትስስር በመፍጠር የአማራ ክልልን የቀውስ ሜዳ ለማድረግ" የጠላት እቅድ በመፈጸምም ሆነ በማስፈጸም ተግባር ላይ ተሳታፊ ናቸው ያላቸው አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠንቅቋል።

የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ ለመጣል በግልፅም ሆነ በህቡዕ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከዚህ ድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነም በማንኛውም አይነት ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።

የመንገድ መዘጋት

ጥቃቱን ተከትሎ መሃል ኢትዮጵያን ከጂቡቲ ወደብ ጋር በሚያገናኘው መስመር ላይ የሚገኘው ከመተሐራ ወደ ወለንጪቲ ከተማ የሚወስደው ዋነኛ መንገድ ለረጅም ሰዓታት ተዘግቶ እንደነበር የአካባቢው ኃላፊዎች ተናግረዋል።

በዚህም ሳቢያ በሁለቱም በኩል የሚያልፉ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ባሉበት ለመቆም ተገደው የነበረ ሲሆን የመከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ተሰማርተው አካባቢውን ካረጋጉ በኋላ መንገዱ ለተሽከርካሪ ክፍት ሆኗል።