ጫንጮ አቅራቢያ ገንዘብ በጠየቁ አጋቾች እጅ የቆዩት የሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች ተለቀቁ

ከአዲስ አበባ በስተሰሜን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለበርካታ ሳምንታት በታጣቂዎች ታግተው የነበሩት የኢትዮ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች መለቀቃቸውን የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገለጹ።

ከአዲስ አበባ በ47 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ጫንጮ ከተማ አቅራቢያ ከሚገኘው የሲሚንቶ ፋብሪካ የምርት ግብዓት ማውጫ ስፍራ በታጣቂዎች ተይዘው የቆዩ ዘጠኝ ግለሰቦች ነበሩ ተብሏል።

የሱሉልታ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ወዬሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በታጣቂዎቹ ታግተው የማስለቀቂያ ገንዘብ ተጠይቆባቸው የቆዩት ዘጠኙ ግለሰቦች ተለቅቀዋል።

ለሳምንታት በዘለቀው በዚህ እገታ በቅድሚያ 27 ሰዎች የሲሚንቶ ፋብሪካው ሠራተኞች ተይዘው የነበረ ሲሆን፣ 18ቱ ከሁለት ሳምንታት በፊት መለቀቃቸውን ተዘግቧል።

በታጣቂዎቹ ተለይተው ከቀሩት መካከል ስድስቱ የሕንድ ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ፣ ሦስቱ አስተርጓሚዎቻቸው እንደነበሩም በወቅቱ ተዘግቦ ነበር።

አቶ ግርማ ታጋቾቹ ተለቅቀው ቀጣሪያቸው ኢትዮ-ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደሚገኝበት የጫንጮ ከተማ መመለሳቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የግለሰቦቹ እገታ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለመሰብሰብ አላማ ያደረገ እንደነበረ የተነገረ ሲሆን፣ አሁን ታጋቾቹ በምን ሁኔታ እንደተለቀቁ ቢቢሲ ከአካባቢው አስተዳዳሪ ማብራሪያ ቢጠይቅም ስለተለቀቁበት ሁኔታ መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ቢቢሲ በታጠቂዎች እገታ ስር የቆዩት ግለሰቦች ቀጣሪ የሆነውን ኢትዮ-ሲሚንቶን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ስልክ ቢደውልም ምለሽ ሳያገኝ ቀርቷል።

"ሕብረተሰቡን በማወያየት እና የፀጥታ ኃይሉን በማጠናከር እንዲህ አይነት ተግባራትን ለማስቆም ጠንካራ ሥራ እየሰራን ነው" ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።

የሲሚንቶ ፋብሪካው ሠራተኞች በታጣቂዎች ከተያዙ በኋላ ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር በመሆን ጥበቃ ሲደርግ ብሎም ታጋቾቹን ለማግኘት መንግሥት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።

አክለውም ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ የፀጥታ ኃይሉ በአካባቢው ተጠናከረ ክትትልና ጥበቃ እያደረገ መሆኑንም አስተዳዳሪው አቶ ግርማ ወዬሳ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ተመሳሳይ እገታና ጥቃቶች ማንነታቸው ባልተገለጸ ታጣቂዎች እንደሚፈጸም ሲዘገብ ቆይቷል።

እንዲህ አይነት ድርጊቶች እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራውና መንግሥት 'ሸኔ' የሚለው በሽብርተኝነት የተፈረጀ ድርጅት የሚፈጽመው መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣንት ቢናገሩም፣ ቡድኑ ግን በእንዲህ ያለው ድርጊት ውስጥ እጁ እንደሌለ ያስተባብላል።