ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምግብ ያለ ዘይት ማብሰል እንችላለን? ባለሙያዎች ምን ይላሉ?
ከሰሞኑ የዘይት ዋጋ መናር የአገሪቱ ሁነኛ አጀንዳ ሆኗል፡፡
ለምን የዘይት ዋጋ በየጊዜው ይንራል የሚለውን አንኳር ጥያቄ ለጊዜው እናቆየው።
ለመሆኑ ያለ ዘይት ምግብ ማብሰል ይቻላል ለሚለው ጥያቄ ምላሽ እንፈልግ፡፡
ዶ/ር ይኹኔ አየለ በዲላ ዩኒቨርስቲ የምግብ ሳይንስና ኑትሪሽን ተመራማሪ ናቸው፡፡
ለእርሳቸው ዘይት በአመዛኙ የአመጋገብ ልማድ እንጂ ከጤና አንጻር እንዲያውም ቢርቀን ነው ጥሩ ይላሉ፡፡
አሁን የተከሰተውን ሁኔታም (A blessing in disguise) በሚል ያስቀምጡታል፡፡ ለበጎ ነው በሚል፡፡
ለዚህ ምልከታ ያበቃቸው የዘይት አገልግሎትና ከዘይት ምን እናገኛለን የሚለውን ከመፈተሸ ነው፡፡
ነገሩን ከሥር መሠረቱ ማስረዳት ሲጀምሩ የምግብ ሳይንስ ዘይትን የሚመለከተው እንዴት ነው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ በመስጠት ይጀምራሉ፡፡
ዘይት ከስሙ ስንነሳ "cooking oil" ነው የሚባለው፡፡ ይህም አገልግሎቱ በዋናነት መቀቀያ/ማብሰያ እንደሆነ አመላካች መሆኑን ነው፡፡
እንደ ማኅበረሰብ የምግብ ሥርዓት ሽግግር ላይ ነን የሚሉት ዶ/ር ይሁኔ ዘየት አሁን ባለው ማኅበረሰባችን አንድ ሁነኛ የምግብ ግብአት ወደ መሆን ተሸጋግሯል ብለው ያምናሉ፡፡
ይህ ደግሞ በከተሞች በይበልጥ ጎልቶ ይታያል፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ በነበረ የምግብ ሥርዓት ዘይት አሁን ያለውን ያህል አገልግሎትና ስፋት እንዳልነበረው ዶ/ር ይኹኔ ያወሳሉ፡፡
‹‹ቅባኑግ የሚባል አለ፤ ከጎመን ዘርና ከቅባት እህሎች እናቶቻችን የሚያወጡት፡፡ እምብዛምም መቀቀያ አልነበረም፤ እንደ ማጣፈጫ ሆኖ ከድቁስ ጋር ተለውሶ ማባያ ነበር የሚሆነው፡፡››
ዘይት ከጤና አንጻር እጅግም አስፈላጊ አይደለም?
ዘይት ለኔ ከተራቆቱ ምግቦች አንዱ ነው የሚሉት ዶ/ር ይኹኔ አገልግሎቱም ብዙ ሰው እንደሚያስበው የምግብ ጣዕም የሚፈልቅበት እንዳልሆነ ያብራራሉ፡፡
"ብዙ ሰው የምግብ ጣዕም ከዘይት የሚመነጭ ይመስለዋል፡፡ ዘይት ጥቅሙ የሚበስለውን ምግብ በቀላሉ ሳይቃጠል በውስጡ የያዘውን ይዞ እንዲቆይ ማስቻል ነው፡፡"
ይህም ማለት ለምሳሌ ጎመን በዘይት እና በውሃ ቀቅለን ብናወዳድረው አረንጓዴ ቀለሙን ይዞ እንዲቆይ፣ ቃናው ተኖ እንዳያልቅ፣ ጠቃሚ ኬሚካሎቹ እንዳይወገዱ ዘይት ሆነኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ የጣዕሙና ቃናው ምንጭ ግን ዘይቱ ሳይሆን ጎመኑ ራሱ ነው፡፡
"የምግብ ጣዕም የመጣው ተነው ሊወጡ ይችሉ የነበሩ ቃናዎች በዘይት አማካኝነት እዚያው መቅረት ስለቻሉ ብቻ ነው፡፡"
ዶ/ር ይኹኔ በሆስፒታሎች ውስጥ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በብዛት ለመታየት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የአመጋገባችን ሥርዓት መቃወስ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
ለዚህ ተጠያቂ የሚያደርጓቸው ስኳርን፣ ጨውን፣ የታሸጉ ምግቦችን፣ በከተሞች የበርገርና የፒዛ ቤቶች መስፋፋት ነው፡፡ ዘይትም አጠቃቀማችን ገደብ የሌለው ከሆነ ለዚህ የጤና ቀውስ አበርክቶት አለው ይላሉ፡፡
ዘይትን በምን ልንተካ እነችላለለን?
ዶ/ር ይኹኔ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዋና መነሻ የኃይል ሰጪ ምግብ (ካሎሪ ኢንቴክ) መብዛት እንደሆነ ካወሱ በኋላ የአኗኗር ባህላችን ደግሞ እንቅስቃሴ አልባ እየሆነ መጥቷል ይላሉ፡፡
ስለዚህ ያ ኃይል ሰጪ ምግብ ተጠራቅሞ ወደ ስብነት ይቀየራል፡፡ ዋናው የዚህ ምንጭ ደግሞ ዘይትና ጮማ ነው፡፡
ዘይትን ማብዛት በሽታን ማብዛት ሆኖ ሊወሰድ ይችላል የሚሉትም ለዚሁ ነው፡፡
በእርግጥ ዘይት ለሰውነታችን በመጠኑም ቢሆን አስፈላጊ እንደሆነ ዶ/ር ይኹኔ አይሸሽጉም፡፡
በተለይ ለአዳጊዎች ዘይት ጠቃሚ እንደሆነ ያወሳሉ፡፡
"ሰውነታችን ሊሰራቸው የማይችሉ አስፈላጊ ፋቲ አሲድ ያላቸው ምግቦች አሉ፡፡ በተለይ ለአዳጊዎች፡፡ የእነርሱም ቢሆን ከአሳ ከወተት ሊተካ ይችላል፡፡"
አንዳንድ ቫይታሚኖች አሉ፤ የቅባት ዘር ስለሆኑ የሚሟሙት በቅባት ነው፡፡ ስለዚህ ዘይት ያስፈልገው ይሆናል ሰውነታችን፡፡ የኛ የቅባት አጠቃቀም ግን የተሳሳተ ነው ይላሉ፡፡
ይህን ሲያስረዱም አንደኛ የዘይት ምጣኔያችን ገደብ አለመኖሩ፣ ሁለተኛ በሁሉም የምግብ ሥርዓታችን ያለ መጠን መካተቱ፣ ሦስተኛ አንድን ዘይት ደግመን ደጋግመን መጠቀማችንን ይተቻሉ፡፡
"ለምሳሌ ጮርናቄ ሲሰራ በአንድ ዘይት ነው የሚሰራው፡፡ ያ ዘይት ወደ ትራንስ ፋት (መጥፎ ስብ) ይቀየራል፡፡ ይህ ደግሞ ለካንሰር ያጋልጣል፡፡"
ዞሮ ዞሮ በዶ/ር ይኹኔ አመለካከት ዘይት ያን ያህልም አስፈላጊ አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ እኛ እንደምናስበው እጅግ ጠቃሚ አይደለም፡፡
ያለ ዘይት ምግብ መሥራት ይቻላል?
ዶ/ር ይኹኔ ይህ ከልማድና ብዙ ዕውቀት ስለሌለ እንጂ ምግቦች ያለ ዘይት ሊዘጋጁ አይችሉም ተብሎ መደምደም ትክክል እንዳልሆነ በምሳሌ ያስረዳሉ፡፡
"ለምሳሌ ድንችን መቀቀል ብንፈልግ በውሃ መቀቀል እንችላለን፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በተልባና በሰሊጥ ወይም በኑግና ሌሎች የቅባት እህሎችን በመጠቀም የቅባት ፍላጎት ማሟላት ይችላል፡፡"
ዶ/ር ይኹኔ ምላሳችን አዲስ ነገርን ለመልመድ ዘለግ ያለ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ይጠቁማሉ፡፡
ሽሮን ያለ ዘይት
ያለ ዘይት ጤናማ ሕይወትን መምራት ይቻላል የሚሉት ዶ/ር ይኹኔ ይህን እንዳናስተውል ያደረጉን አመለካከትና ልማድ እንደሆኑ ያብራራሉ፡፡
እንደ ምሳሌ የሚያነሱት ሽሮን ነው፡፡
ለምሳሌ ሽሮን ያለ ዘይት መሥራት ይቻላል፡፡ ሽሮ የሚጣፍጠው በዘይት አይደለም፡፡ ዕውቀቱ ነው የሌለን፡፡ ሽሮን በተልባ መሥራት ይቻላል፡፡ እናቶቻችን በኑግልጥ በተልባ ሠርተውታል፡፡ ምንም ምግብ ያለ ዘይት ይቻላል፡፡
እስክንለምደው ሊያንገዳግደን ይችላል እንጂ ይቻላል፡፡
በኮሰረት የተነጠረ ቂቤ ከየት ይመጣል አትበለኝ እንጂ ሽሮ የምትጣፍጠው በዘይት ነው በቂቤ? ብለው ይጠይቃሉ፡፡
ይህን ይህን ካወሳሱ በኋላ የሥነ ምግብ ተመራማሪው ዶ/ር ይኹኔ እንዲህ ሲሉ ይደመድማሉ፡፡
"ንገረኝ ካልከኝ፣ ዘይት ቢቀር ብዙም ከማይቆጫቸው ሰዎች መሀል አንዱ ነኝ፡፡"