የኢትዮጵያ እናቶች "ለወላጆች ጥቅም ሲሉ" በቁጥጥር ሥር ያዋሉት የፌስቡክ ገጽ

ፌስቡኩ በአመዛኙ ታውኳል። በጥላቻ ፖለቲካ እና አታካሮ ተሞልቷል።

የእናቶች ገጽ ላይ ሲደረስ ግን ፈውስ ይገኛል። ወጀቡ ይሰክናል። ጡዘቱ ይረግባል።

ለምን ቢባል አንደኛ "ማሚዎች" ለትንኮሳና ስድብ አይመቹም። ፌስቡክ በአመዛኙ የመዘነጣጠል አውድማ ነው።

ሁለተኛ "ማሚዎች" ጥምዝ ፖለቲካን አያውቁም።

ይዘቶቻቸውም ቢኾን እጅ እጅ አይሉም፤ ሰው ሰው እንጂ።

"ልጄን በሰላም ተገላገልኩ! ደስ ብሎኛል፤ ደስ ይበላችሁ" ለምትል እናት የሚሆን ስድብ ያለው ሰው ካለ እጁን ያውጣ።

በቃ ልክ እንደዚያ ማለት ነው።

ማሚዎች፣ በፌስቡክ ጫካ የሚንቦገቦገውን የአሉታዊነት እሳት ውሃ ይቸልሱበታል።

"ማሚዎች ጉድ ሆንኩላችሁ፣ አታምኑኝም፣ ፔሬዴ ቀረላችሁ" ከምትል ኮረዳ ጀምሮ፤ "በልጅ ፍቅር መሞቴ ነው፣ መውለድ ግን አቃተኝ፣ በፀሎታችሁ እርዱኝ" እስከምትለዋ፤ በውድቅት ሌሊት ውድ ልጇ በቶንሲል ታሞባት "ማሚዎች ድረሱልኝ" ብላ የፌስቡክ ሰፈር ኡኡታ ከምታሰማ ምስኪን እናት፣

"ባሌ እንደሚወደኝ እርግጠኛ መሆን አልቻልኩም፣ ሰሞኑን እንደ ድሮ ጥብቅ አድርጎ አያቅፈኝም" እስከምትል ገራገር ሚስት ድረስ፤ በርካታ እናቶች ይሳተፉበታል።

የእናቶች ስክነት ዲሽቃ ያበርዳል፡፡

ሰሞኑን ግን ባሎችም ተጋብዘዋል፡፡ ባሎች ግን ባይጋበዙ አይሻልም ነበር?

ባሎች ለምን መጡ ግን? ባሎች ከፈለጉ የራሳቸውን ገጽ ለምን አይከፍቱም? በእናቶች የፌስቡክ ሰሌዳ ላይ ምን ያስቸከችካቸዋል?

በዚህ ላይ አጥጋቢ መልስ ለማግኘት ከእናት ሩታ ጋር ወደ በኋላ ላይ እናወጋለን።

ሩታ ተረፈ የእናቶች ገጽ "እናት" ናት። እናት ባንላት እንኳ "አክስት" ናት።

ምክንያቱም የዚህ ገጽ የመጀመርያዋ መሥራች እሷ አደለችም።

ይቅርታ!

ሐተታችን ግር ያለው ካለ ስለ "የእናቶች ወግና አስተዳደግ የፌስቡክ ገጽ" ነው የምናወራው።

ይህ ገጽ በአንዲት ለጊዜው ስሟ ባልተገለጸ እናት ነበር የተጀመረው። በግንቦት ወር፣ 2012 ዓ.ም የተወለደው።

ከጊዜ በኋላ ፌስቡክ አንድ መልዕክት ላከ።

"ይህ ገጽ አስተዳዳሪ የለውም፤ ልዘጋው ነው" የሚል።

ይህ መልዕክት ለማን ይደርሳል? ለቲና ተረፈ።

በዚህ ወቅት ቲና ከገጹ አጋፋሪዎች (Moderators) አንዷና ምናልባትም ብቸኛዋ ነበረች።

ፌስቡክ ደግሞ ማሳሰቢያ ላከ፤ 'ይህን ገጽ ታስቀጥይዋለሽ ወይስ እንደሞተ እንቁጠረው?' የሚል።

በዚህና በሌሎች ውስብስብ ውስጣዊ ጉዳዮች የተነሳ ገጹ በታሪክ አጋጣሚ ቲና እጅ ላይ ወደቀ።

"አጋጣሚ ቢሆንም ግን የገጹን ሕልውናውን የታደግኩት እኔ ነኝ" ትላለች።

እስኪ ስለ እናት ቲና ተረፈ በአንድ ገጽ እናውራ፡፡

ቲና ነዋሪነቷ በአሜሪካ ቢሆንም ዜግነቷ 'ፌስቡካዊ' ነው ማለት ይቀላል፡፡

ረዥሙን ጊዜዋን የምታጠፋው ይህን ገጽ በማስተዳደር ነው፡፡

ፊትና ፋታ በማትሰጠው የውክቢያዋ ምድር- አሜሪካ ሆና ሁለት ልጆቿን እያሳደገች፣ ይህን ገጽ ደግሞ እንደ ሦስተኛ ልጅ ትንከባከባለች፡፡

የእውን ልጆቿን ትምህርት ቤት አድርሳ ስትመለስ የምናባዊ ዓለም እናትነቷን ትቀጥላለች፡፡ በፌስቡክ፡፡

እሷ ግን፣ "እኔ ብቻ አይደለሁም መመስገን ያለብኝ፤ ከገጹ ጀርባ 13 ጠንካራ እናቶችና 1 አባት በታታሪነት ተሰልፈዋል" ትላለች፡፡

እስኪ ለ400 ሺህ ሩብ ጉዳይ የሆነ ሕዝብ የሚከተለውን "የእናቶች ወግ" የተሰኘውን ገጽ ዘልቀን እንፈትሸው፡፡

ከመድረክ ጀርባ ምን አለ?

ከመድረክ ጀርባ ብዙ ነገር አለ፡፡

ለካንስ ዋናው የእናቶች ታሪክ እኛ በየዕለቱ ተለጥፎ በምናነበው ቁርጥራጭ ልጥፍ የሚገለጽ አይደለም፡፡

ለካንስ "ያገለገለ ፍሪጄን ግዙኝ" በሚል ልጥፍ ይህ ገጽ የሚገለጽ አይደለም፡፡

እነ 'ማሚ' እኮ ብዙ ነገር ይደብቁናል፡፡

የማኅበራዊ ህይወት መዳከም

በቀድሞ ዘመን በተለይ ለእናቶች "የቡና ጠጡ" ሥርዓት ነበር፡፡

አንዳንድ የአዲሱ ትውልድ አባላት "በቀድሞ ዘመን" ስንል ስለ አጼዎች ዘመን የምናወራ ሊመስላቸው ይችላል፡፡

ስለ ቅርብ ታሪክ ነው የምናወራው፡፡

በቀድሞ ጊዜ በቡና ዙርያ ማኅበራዊ ሕይወት ይደራል፡፡ ልጅ ይታቀፋል፡፡ እናቶች የጎንዮሽ መረጃ ይለዋወጣሉ፡፡ ባል ሸንቆጥ ይደረጋል፡፡

ደግሞስ ብትሉ፣ ለግል ጭንቀት የጋራ መላ ይመታል፡፡ አንዳች ዓይነት የጋርዮሽ ብርታት (Social Psychiatry) ነበረ ማለት ይቻላል፡፡

ከዚያ ድንገት በከተሜ አኗኗር ዘመነ ተባለ፡፡ በፎቅ ላይ ቡና አይወቀጥም ተባለ፡፡ ኮንዶሚንየሞች በዘነዘና መራድ ጀመሩ፡፡ የነዋሪዎች ኮሚቴ መቆጣት ጀመረ፡፡ ቡና ቀጠነ፡፡

ሌላ ሰፈር ደግሞ አጥር ዘለግ ተደርጎ መታጠር ዘይቤ ሆነ፤ ቤቶቹ በቡዳ እንዳይበሉ የተፈራ ይመስል፡፡

ጎረቤታሞች የቅርብ ሩቅ ሆኑ፡፡ የፈጣሪ ሰላምታን መለዋወጥ ፈሩ፡፡

የቡና ዙርያ የእናቶች ወግ እየከሰመ መጣ፡፡ ዘመናይ እናቶች ዘመናይ ስልክ ይዘው መጡ፡፡

ማኅበራዊ ሕይወት በስልክ ዳበሳ ሆነ፡፡ "በሽልም ታውጣሽ" በኢሞጂ ተተካ፡፡

ይህን የማኅበራዊ መስተጋብር ሽንቁርን ለመሙላት ይህ የፌስቡክ ገጽ ተወለደ፡፡

ገጹን ለወላጆች ጥቅም ሲባል የኢትዮጵያ እናቶች በቁጥጥር ሥር አዋሉት፡፡

እናት ቲና ተረፈ፣ "ማኅበራዊ እሴታችንን ይዘን ነው ወደ ፌስቡክ የዘለቅነው" የምትለው ለዚህ ነው፡፡

"ለኔ እያንዳንዷ እናት ጀግና ናት"

"የምር ግን እናቶች የሆድ የሆዳችሁን ታወሩበታላችሁ እንዴ?" ለሚለው የቢቢሲ ጥያቄ ቲና ተረፈ መልስ ከመስጠት ይልቅ ከፌስቡክ ጀርባ በውስጥ መስመር የሚላከውን ሺህ መልዕክት ማስቃኘት ትመርጣለች፡፡

ለካንስ ትልቁ ታሪክ ያለው በውስጥ መስመር ነው፡፡ ለካንስ እኛ የምናየው ቧልት ቧልቱን ነው፤ ገብስ ገብሱን፡፡

ሁለት አብነቶቿ የእናቶችን ዓለም ይገልጥልን ዘንድ እናት ቲናን ለአፍታ እንስማት፡፡

"ለምሳሌ በብቸኝነት ሊያብዱ የደረሱ ይገጥሙናል፡፡ ራሳቸውን ማጥፋት የሚሹ፣ ነገር ግን ለውሳኔ ውልውል ውስጥ የገቡ እናቶች ይገጥሙናል፡፡

"በተለይ ይህ የሚሆነው ከድኅረ ወሊድ ድብታ (Postpartum Depression) ጋር ተያይዞ ነው፡፡ የሚጽፉልን ነገር እጅግ ያስደነግጠናል" ትላለች፡፡

"የ6 ወር ልጄን ግደይው ግደይው ይለኛል"

"አንዲት እናት ጻፈችልኝ፡፡

'የ6 ወር ልጄን ግደይው ግደይው ይለኛል' አለችኝ፡፡ ደነገጥኩ፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ገባኝ፡፡

'ይቅርታ እህቴ ልደውልልሽ? ይሄ በቴክስት የሚወራ ነገር አይደለም' አልኳት፡፡

'የት ነው ያለሽው አሁን?'

'ቤቴ'

'እስኪ ወደ ደጅ ውጪ እህቴ"

'እሺ!'

'ምን ይታይሻል?'

'ብርሃን ይታየኛል፡፡'

እንዲህ እንዲህ እያልን ረዥም ሰዓት ብዙ ነገር አወራን፡፡

ስትረጋጋ የሥነ ልቦና ባለሙያ ማየት እንዳለባት ነገርኳት፡፡ ብዙም ፍቃደኛ አልሆነችም፡፡

በየቀኑ እየደወልኩላት ቀስ በቀስ ተግባባን፡፡

ታሪኳን ስትነግረኝ አጠገቧ ሰው የለም፡፡ በትዳሯ ደስተኛ አይደለችም፡፡

እንዲህ መጥፎ ሐሳብ ወደ አእምሯ እየገባ የሚያስቸግራት ለካ አጠገቧ ሰው አጥታ ነው፡፡ ሰው ተርባ ነው፡፡ ወደኛ ገጽ ያመጣትም ይኸው ነበር፡፡

'ከዚያ በኋላ የሆነ ቀን ምን አለችኝ፡ 'ቲናዬ የሚገርምሽ ነገር፣ ያ ልጄን ግደይው ግደይው የሚለኝ ስሜት እኮ ድንገት ከውስጤ ጠፋ።'

'ለካንስ ልጄን እንደዚህ እወደዋለሁ' አለችኝ፡፡

እንደዚያ ዕለት በዚህ የእናቶች ወግ ገጽ ፋይዳ ተደስቼ አላውቅም፡፡ አንዳንዴ እንዲህ በሐሴት የሚሞሉን ታሪኮች ይገጥሙናል፡፡"

ሌላ እናት ደግሞ ጥልቅ ችግር ውስጥ ገብታ "በቃ አልቻልኩም፤ አሁን ራሴን ማጥፋት ብቻ ነው የምፈልገው" አለችኝ፡፡ በውስጥ መስመር፡፡

"መሞት እኮ ቀላል ነው፡፡ ግን ልጅ ያላት እናት ራሷን ታጠፋለች እንዴ? ራስ ወዳድ ከሆንሽ ራስሽን አጥፊ" አልኳት፡፡

ስናወራ እየቀለላት መጣ፡፡

"ልጅሽ እኮ ከምግብ በላይ አንቺ ታስፈልጊዋለሽ፡፡ ብታቅፊው ራሱ ይጠግባል" ስላት አለቀሰችና ተረጋጋች፡፡

ከዚህ በኋላ መፍትሄ ፈለግንና የተሻለ ነገር እንድታገኝ ተደረገ፡፡ ባለሙያ እንዲያማክራት አደረግን፡፡"

"ትዳሬን ትቼ ልወጣ በር ላይ ቆሜ ነው የምጽፍላችሁ"

ብዙ ሰው የሰው ችግር 'ችግር' ሆኖ አይሰማውም፤ እስኪደርስበት ድረስ፡፡

ለምሳሌ፣ "ልጄን እንጥሉን ላስቆርጠው ወይ?"

"ሴት ልጄን ላስገርዛት አስቤ ነበር፤ እርዱኝ፡፡"

"የ2 ወር ልጄ አልፋፋ አለኝ ምን ላብላው?" የሚሉ አስደንጋጭ ጥያቄዎች ከእናቶች ይመጣልናል፡፡

ብዙ ሰው ግን ይሄ እውነት ላይመስለው ይችላል፡፡

ሌላ ጊዜ ደግሞ "ልጄ ቶንሲል ይዟታል፤ መብላት መተንፈስ አትችልም፡፡ ትኩሳቷ በጣም ከፍ ብሏል" ያለችን እናት ቶሎ ሐኪም ቤት ውሰጃት ስንላት ግን ዳተኛ ነበረች፡፡

በስንት መከራ ወዲያው ሐኪም እንድታይ አግባብተናት ልጇ እንድትተርፍ አጋጣሚ ሆነናል፡፡

አንዳንዴ፤ አሁን ይቺ እናት ወደኛ ባትጽፍ ምን ሊከሰት ይችል ነበር ብዬ እደነግጣለሁ፡፡ ለሆኑ ሰዎች የመጀመርያ እርዳታ መስጠት ችለናል እንዲል የሚያስችለኝ ይሄ ይሄ ነገር ነው፡፡

አሁን ብዙ ሰው የሚያስበው ቶንሲል ከሆነ ሐኪም ቤት መሄድ ነው ምን ማካበድ ያስፈልጋል ብሎ ያስባል፡፡ ቶንሲል አደገኛ እንደሆነ የማያውቁ በጣም ብዙ እናቶች እንዳሉ አይረዳም፡፡

እናት ለእናት ግን ሲሆን ችግሩ ቶሎ ይገባናል፡፡ ሕመሞቻችን ብዙዎቹ የጋራ ናቸው፡፡

"ትዳሬን ትቼ ልወጣ በር ላይ ቆሜ ነው የምጽፍላችሁ" የሚሉ ብዙ ተሞሻሪዎች አሉ፡፡

ለምን እንደዚያ ሊሉ እንደሚችሉ ይገባናል፡፡

'ኑሮን መቋቋም አልቻልኩም፤ አስቤዛ መግዛት አቃተኝ፣ ቤቴ እያየሁት ላዬ ላይ ሊፈርስ ነው' የሚሉን እናቶች አሉ፡፡ ምን ማለታቸው እንደሆነ ይገባናል፡፡

ሁሏም እናት ጭንቀቷን በሆዷ ይዛ ነው የምትኖረው፡፡ ለቤተሰቧ እንኳ አታጋራም፡፡ ለእናቶች ስታካፍል ነው እፎይታ የምታገኘው፡፡

ለምሳሌ ጽንስ የጨነገፈባቸው እናቶች አሉ፡፡ በጣም ስሜታቸው ይሰበራል፡፡ በውስጥ መስመር ስናወራቸው ይድናሉ፡፡

ተመሳሳይ አጋጣሚዎች በኛም በሌላም እናት ደርሶ እንደነበር ስንነግራቸው እፎይታ ይሰማቸዋል፡፡

በችግር ውስጥ ያለ ሰው ዓለም ትደፋበታለች፡፡ ችግሩን አግዝፎ ነው የሚያው፡፡

ቅንጣት ችግር እርዳታ ባለማግኘት ብቻ ተራራ ትሆናለች፡፡ እኛ 'በእናቶች ወግ' ትንሽዋን እርዳታ ለመስጠት ነው የምንሞክረው፡፡

"እናቶች ችግራችን ተቀራራቢ ነው፡፡ እኔ ጋር ያለው ችግር ያቺኛዋ እናትም ጋር አለ፡፡ ወይ የትዳር ጉዳይ ነው፣ ወይ የልጅ ጉዳይ ነው፡፡ ወይ ጭንቀት ነው፡፡ ብቻ የኛ የእናቶች ጭንቀት የወል ነው፡፡ እናትነት ስለሚያመሳስለን እንቀራረባለን" ትላለች ቲና፡፡

"ለባሌ ሥራ ፈልጉለት"

ይህ የእናቶች ወግ ገጽ ከሥነ ልቡና መደጋገፍ ባሻገር አንዳንዴ በገቢር መተጋገዙም ይበረታል፡፡

ለምሳሌ ልጄን ማሳደጊያ ገቢ የለኝም ለምትል እናት ተሯሩጦ ሥራ ፈልጎ የመስጠት አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

"ለባሌ ሥራ ፈልጉለት" የምትል እናት ስትመጣ የራሳቸው ቢዝነስ ያላቸው ሰዎች፣ የድርጅት ሥራ አስፈጻሚ የሆኑ የገጻችን አባላት ወዘተ የሚችሉትን ያደርጋሉ፡፡

"ምንድነው የተማረው፡፡ እኔ እህቴ ጋ አስቀጥረዋለሁ ወዘተ" ተባብለው መፍትሄ ይሰጣሉ፡፡

"በጣም ለተቸገሩ እናቶች ራሱ ስፖንሰር አፈላልገን ሥራ እንዲጀምሩ አድርገን እናውቃለን" ትላለች ቲና፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ልጆቻቸውን ለማሳከም የሚያቅታቸው እናቶች ከግል ሐኪም ቤቶች ጋር ተነጋግረው እንዲታከሙ አድርገዋል፡፡

የሕግ ማማከር እርዳታን የፈለጉ እናቶችም እንዲሁ፡፡

ለጠበቃ የሚከፈለው ገንዘብ ሲያቅታቸው እዚያው ሕግ የተማረች እናት፣ የኛ ገጽ ተከታታይ ትመጣና፣ "ነይ ችግር የለም፤ እኔ ነጻ የሕግ አገልግሎት እሰጥሻለሁ" ትላታለች፡፡ በውስጥ መስመር ተገናኝተው ይረዳዳሉ፡፡

"አንዳንዴ ይሄ ገጽ ተራ የፌስቡክ ገጽ ሳይሆን ተቋም ሆኖ የሚታየኝ ይሄን የመተጋገዝ ስሜት ስመለከት ነው" ትላለች ቲና፡፡

ስሜታቸውን የሚጋራላቸው ሰው ስላገኙ ብቻ የሚያለቅሱ እናቶች

"መውለጃዬ ደርሷል፣ እባካችሁ መርቁኝ" የሚል የፌስቡክ ልጥፍ ለብዙ ሰው ቀላል ይመስላል፡፡

በተለይ ወንዶች በዋዛ ያዩት ይሆናል፡፡ ተላላነትም ሊመስላቸው ይችላል፡፡

ለዛች ሴት ግን የሚሰማት ስሜት እንደዚያ አይደለም፡፡

ሁለት ሺህ ሰው አይዞሽ እያለ ሲመርቃት እንባዋን ማቆም ሁሉ ሊያቅታት ይችላል፡፡ የደስታ እንባ፡፡ ብቻዬን አይደለሁም የሚል እንባ፡፡

ያቺው ሴት ከተገላገለች በኋላ ደግሞ ተመልሳ ትመጣና፣ "ይኸው ጤነኛ ልጅ ወለድኩኝ፤ እስኪ ልጄን መርቁልኝ፤ እንትፍ እንትፍ!" ትላለች፡፡

ሺህ እናቶች ይመርቋታል፡፡ ያን ሺህ ምርቃት ማንበብ ለአንዲት የወለደች እናት ምንኛ ደስ የሚል ስሜት እንደሚያሳድር ለማወቅ እናት መሆን ያስፈልጋል፡፡

ብዙ እናቶች ከወሊድ በኋላ ለድኀረ ወሊድ ድብታ ይጋለጣሉ፡፡ ይህን የሚረዳ ባል ከስንት አንድ ነው፡፡

እናቶች ግን ይግባባሉ፤ የጋራ ነዋ ጉዳዩ፡፡ ስለዚህ አይዞሽ የኔ ቆንጆ ይባባላሉ፡፡

ይህ ለብዙ ወንዶች ላይገለጥላቸው ይችላል፡፡ ለእናቶች ግን ከሞት ወደ ሕይወት የሚያመጣ ተአምር ነው፡፡

ቲና ይህን ሐሳብ ስታጠናክር እንዲህ ትላለች "እኛ ራሳችንን የምንመለከተው እንደ አንድ ቤተሰብ ነው፡፡ በውስጥ ስናወራ በቃ ጓደኛሞች ነን እንጂ ዝም ብሎ አጋጣሚ ፌስቡክ ያገናኘን ባዕድ ሰዎች አይደለንም፡፡"

"አርግዣለሁ-አላረገዝኩም" በድምጽ ብልጫ

በማሚዎች የፌስቡክ ሰሌዳ የሚጻፉ ልጥፎች አንዳንዶቹ ፈገግታን ይጭራል፡፡

ለምሳሌ በቀደም'ለታ አሮጌ ፍሪጅ በ6ሺህ ብር ግዙኝ ብላ የለጠፈች እናት ላይ የተቀለዱ ቀልዶች ፍሪጁን ራሱ ወደ በረዶነት የሚቀይሩ ነበሩ፡፡

ሌላኛዋ ደግሞ ፈጣን የእርግዝና ምርመራ አድርጋ፣ "ማሚዎች አርግዣለሁ ወይስ አላረገዝኩም?" ስትል መድረኩን ክፍት አድርጋው ነበር፡፡

ሺህ ሕዝብ ፍርድ ሲሰጥ አመሸ፡፡

ግማሹ አልትራሳውንድን በሚያስንቅ እርግጠኝነት "አርግዘሻል እንኳን ደስ ያለሽ" ሲላት፤ ግማሹ "ኧረ በፍጹም!" ይላል፡፡

ይሄ ነገር በድምጽ ብልጫ የሚወሰን ጉዳይ ነው እንዴ? ያሰኛል፡፡

"ልጄን አተኮሳት" ለምትል እናትም በፌስቡክ የሕዝብ ድምጽ የልጇን ሕመም ለመጠቆም የሚሞክር ብዙ ነው፡፡

ይሄ የተርታ ሕዝብ ምክር ታዲያ አደጋ አይኖረውም? አንዳንድ ጉዳዮች በባለሙያ ብቻ ቢመከሩ አይሻልም?

እናት ቲና ተረፈ በዚህ ረገድ ጥብቅ ፖሊሲ እንደሚከተሉ ታወሳለች፡፡

"እኛ ሁልጊዜም የመጀመሪያ እርዳታ ሰጪዎች ነን እንጂ ባለሙያን አንተካም" ትላለች፡፡

"አደጋ የደረሰበት ሰው የመጀመሪያ እርዳታ በጊዜው ባለማግኘቱ ሊሞት ይችል የለ? እኛ በቃ ያንን ነው የምንሰጠው፡፡"

በእናቶች ወግ ገጽ አባል የሆኑ የሕግ፣ የጤና፣ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች እንደ ቤተሰብ አብረዋቸው አሉ፡፡ "እነሱን ቢሆን የመጀመሪያ እርዳታ ነው የሚሰጡት፡፡"

ሆኖም ግን ከመድኃኒትና ሕክምና ጋር በተያያዘ ገጹ ላይ ጥያቄ መጠየቅም ሆነ አስተያየት መስጠትን አናበረታታም ትላለች የገጹ የበላይ አስተዳዳሪ፡፡

"የኛ ፔጅ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ አራስ ሕጻናት አሉ፤ ነፍሰ ጡር እናቶች አሉ፡፡ እንደ ዋዛ የሚሰጥ ምክር ሰምተው እንደዋዛ ለአደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ አንድ ፌስቡክ አስተያየት ሕይወትን ለአደጋ ሊያጋልጥ ስለሚችል በመድኃኒት ዙርያ ልጥፍን አግደናል፡፡"

14ቱ የእናቶች ወግ ገጽ አጋፋሪዎች

በቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥያቄዎች የሚደርሱት ይህ ገጽ ለአስተዳዳሪዎቹ ፋታ የሚሰጥ አይደለም፡፡

"እዚህ አሜሪካ ሌሊት ሲሆን አገር ቤት ቀን ነው፡፡ 11 ሰዓት ልዩነት አለ፡፡ አስቸኳይ ጉዳይ የሚያጋጥማቸው እናቶች ብዙ ስለሆኑ ብዙ ጊዜ ሌሊት ቁጭ ብዬ መልስ እየሰጠሁ ነው የማመሸው" ትላለች ቲና፡፡

ከእርሷ ጋር አብረው እየተፈራረቁ የሚሠሩ 12 ሴቶችና 1 ወንድ አለ፡፡

ደምበኛና መደበኛ ሳምንታዊ ስብሰባ ያደርጋሉ፡፡ ቃለ ጉባኤ ይይዛሉ፡፡ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ይወያያሉ፡፡

በጤና ጣቢያና በትምህርት ቤቶች እየተገኙም ስልጠና ይሰጣሉ፡፡

ወደፊት ይህን ገጽ ወደ ቴሌቬዥንና ራዲዮ የማሳደግ ሕልማቸውን በዩትዩብ አንድ ብለው ባርከውታል፡፡ ወደ ተቋምነት ለማድረስም እየሠራን ነው ይላሉ፡፡

አሁን ይህ ገጽ ዓይኑን በዓይኑ ለማየት በቅቷል፡፡ መልካም ቤተሰብና ልጆች አስተዳደግ የሚል ወደ 50ሺህ ተከታይ ያለው ሌላ ገጽ ወልዷል፡፡

አንዳንድ ወንዶች በእናቶች ገጽ መጥተው መሳተፍ ይፈራሉ፡፡ አማራጫቸውን ለማስፋትም ስንል ነው ተጨማሪ ገጽ የከፈትነው ትላለች ቲና፡፡

ባሎች ለምን የእናቶች ገጽ ላይ ይጋበዛሉ?

ባሎች ፈራ ተባ እያሉም ቢሆን ወደዚህ ገጽ እየመጡ ነው፡፡ ወደ እናቶች ወግ!

አሁን አሁን ደግሞ ሚስቶቻቸው እየጋበዟቸው ንቁ ተሳታፊ እየሆኑ ነው፡፡ ይሄ መልካም ነገር ነው?

አይበጠብጧችሁም? ግን እንዳይገቡ ቢደረግ አይሻልም?

ቲና ባሎች/አባቶች ወደዚህ ገጽ እንዲጋበዙ የሆነበት ምክንያት ስታስረዳ በሚስቶች አማካኝት እንደሆነ ታወሳለች፡፡

ይሄ ፔጅ ሱስ ሆኖብኛል የሚሉን እናቶች ብዙ ናቸው፡፡ ባሎቻቸውን የሚጋብዙት እነሱ ናቸው፡፡

እኔ የማሳልፈውን ሕይወት ባለቤቴ ይጋራኛል፡፡ ብዙ ታሪክ እናነባለን፡፡ ባሎች እነዚያን ታሪኮች በማንበብ ለሚስቶቻቸው ምን ያህል ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ (Emotional support) ማድረግ እንዳለባቸው ይረዳሉ ብለው በማመናቸው ነው፡፡

የሚስቱን ድካም የማይረዳ ባል ይኖራል፡፡ ሚስቱ ቤት መዋሏ ስንፍና የሚመስለው ባል ሊኖር ይችላል፡፡

የእናቶችን ድካም ሲረዳ፣ እናቶች የሚጽፉትን ሲያነብ፣ ልጅ ማሳደግ ቀላል እንዳይደለ፣ ቤት ቀጥ አድርጎ መምራት ቀላል እንዳይደለ፣ እና ሌሎች ተራ የሚስመሉ እናቶች የሚያጋጥሟቸው የስሜት ስብራቶችን እየተረዳ ይመጣል፡፡

በመጨረሻም ካለእናት ልጆች የሚያሳድጉ አባቶች (የሲንግል ዳዶች) ነገር፤ የሲንግል ማሚዎችን ዓይነት ሲንግል ዳዶች ይህን ገጽ እንደሚወዱት ቲና በማስረጃ ትናገራለች፡፡

ብቻቸውን ልጆቻቸውን እንደ እናት የሚያሳድጉ አባቶች አሉ፡፡

"ለምሳሌ ልንገርህ! ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖር አንድ ወንድም ነበረን፡፡ በእኛ ገጽ ብዙ ፖስት ያደርጋል፡፡ ኋላ ላይ የሁላችንንም ትኩረት አገኘ፡፡

"ታሪኩን ሲነግረን ያሳዝናል፡፡ ባለቤቱ ነፍሰ ጡር ሆና ሳለ መኪና እየነዳች አደጋ ደርሶባት ፓራላይዝድ ሆነችበት፡፡ ልጅ የማሳደጉ ነገር እሱ ላይ ወደቀ፡፡ ወደ እናቶች ወግ በመቀላቀል ባለቤቱንና ልጁን እንዴት መንከባከብ እንዳለበት ተማረ፡፡

በኋላ ባለቤቱ አረፈች፡፡ እሱም የአንድ ዓመት ልጅ ይዞ ቀረ፡፡ አሁን የገጹ ቋሚ ተሳታፊ ነው፡፡

"እንደዚህ ዓይነት ነገር ስሰማ ወንዶች የገጻችን አባል መሆናቸው በጎ ገጽታ እንዳለው በደንብ እያመንኩ መጥቻለሁ" ትላለች እናት ቲና ተረፈ፡፡

ከነቲና ጋር ሆኖ ገጹን ከሚያስተዳድሩት 13 ሹማምንት አንዱ ወንድ ነው፡፡

"እጅግ ጠንካራ አባት፣ ሚስቱን የሚወድ ባል፣ የኛ ደግሞ መከታና አለኝታ ወንድማችን ነው፡፡ እሱን ስናይ ብዙ ባሎች ወደዚህ ገጽ መምጣት እንዳለባቸው ይሰማናል" ትላለች ቲና፡፡

"መፈንቅለ ገጽ" እንደማያደርጉ በመተማመን፡፡