ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለዓመታት በቁም እስር ላይ የነበሩት የኤርትራ የቀድሞ ፓትርያርክ ማረፋቸው ተገለጸ
ለዓመታት በቁም እስር ላይ የነበሩት የቀድሞ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ እንጦንዮስ ማረፋቸውን ቢቢሲ ከሰሜን አሜሪካ ሃገረ ስብከት ካገኘው መረጃ መረዳት ችሏል።
የቀድሞውን ፓትርያርክ የሚደግፈው የሰሜን አሜሪካ ቤተ ክርስትያን ሃገረ ስብከት አባል ሊቀ ካህናት ገብረ ሚካኤል ዮሃንስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አቡነ እንጦንዮስ ረቡዕ ጥዋት፣ የካቲት 2፣ 2014 ዓ.ም አርፈዋል።
አቡነ እንጦንዮስ የ97 አመት እድሜ ባለጸጋ ነበሩ።
አስከሬናቸው ወደ ደቡባዊ ዞን ሰፍዓ በተባለ ቦታ ወደ ምትገኘው አባ እንድርያስ ገዳምም በትናንትናው ዕለት ተወስዷል።
በዩናይድ ኪንግደም የሚገኙ የአባ እንጦንዮስ ተከታይ የሆኑት አባ ዮሃንስ ገብረህይወት በበኩላቸው እረፍታቸውን አረጋግጠዋል።
"ቅዱስ እንጦንዮስ ከ16 አመታት በላይ በእስር ቆይተዋል። ላመኑት አምላክና ቃል ለገቡት ቤተ ክርስቲያን ሲሉ በሰማዕትነት እስር ላይ እያሉ አርፈዋል" ብለዋል አባ ዮሃንስ
አቡነ እንጦኒዮስ ለረጅም ጊዜ የኤርትራ መንግሥት በእምነት ላይ የሚያደርውን ጣልቃ ገብነት ሲተቹ የቆዩ ሲሆን፤ በዚህም ለ16 ዓመታት ያህል ከመንበራቸው ተነስተው በቁም አስር ላይ መቆየታቸው ይነገራል።
በአውሮፓውያኑ 2006 ከመንበረ ፓትርያርካቸው እስኪወርዱ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ በሶስተኛ ፓትርያርክነት አገልግለዋል።
ከሶስት ዓመት በፊት የኤርትራ ሲኖዶስ የቀድሞውን ፓትሪያርክ "በመናፍቅነት" አውግዘው ከመንበራቸው በማንሳት የእምነቱ ተከታዮች "እውቅና እንዳይሰጧቸውና ስማቸውንም እንዳያነሱ" አዘው ነበር።
ፓትሪያርኩ ከቤተክርስቲያኗ አባልነት የተገለሉ ቢሆንም በቤተክርስቲያኗ ባለቤትነት ስር በሆነ ቤት ውስጥ እንዲኖሩ ተፈቅዶላቸው ነበር።
በግዞት ላይ ባሉ ተከታዮቻቸው አማካኝነት ከሶስት ዓመት በፊት በተለቀቀ ቪዲዮ ላይ ክሱን ውድቅ በማድረግ ከቤተ ክርስቲያኗ እንዲወጡ መደረጋቸውንም አልተቀበሉም።
በዚህ ቪዲዮ፤ ፓትርያርኩ መጀመሪያ ላይ ከመንግሥት ጋር ስለተፈጠረው አለመግባባት ሲያብራሩ፤ አቶ ዮፍታሔ ዲሞጥሮስ የተባሉ ከመንግሥት የተላኩ ሰው ቤተክርስትያኒቱን እመራለሁ ብለው እንደመጡ፤ እሳቸው ግን ቤተክርስቲያኗ ዲያቆን ወይም ቄስ ባልሆነ ሰው መመራት እንዳማትችል ገልጸው መቃወማችውን አብራርተዋል። ሆኖም አቶ ዮፍታሔ፤ ሃሳባቸውን እንዳልተቀበሉ በአጽንኦት አስረድተው ነበር።
አቡነ እንጦንዮስ ይህንን ሃሳብ ወደ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ ባቀረቡበት ጊዜም የሲኖዶሱ አባላት ''መንግሥት ከወሰነ እኛ ምን ማድረግ እንችላለን?'' ብለው እንደመለሱላቸው አስረድተዋል።
ኋላ ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ በስድስት ወንጀሎች እንደከሰሳቸው የሚናገሩት አቡነ እንጦንዮስ፤ ''ሕግ በመጣስ እኔን ሳያናግሩ ራሳቸው ከሳሽና ፈራጅ በመሆን ከፓትርያርክነት አውርደው ተራ መነኩሴ እንድሆን አደረጉኝ'' ሲሉ ሁኔታውን በወቅቱ አብራርተዋል።
የቁም እሥረኛ እንዲሆኑ ከተደረገ በኋላ የጸጥታ ኃይሎች እና አንድ ካህን ወደታሠሩበት ቤት በመሄድ፤ መስቀል፣ መጻሕፍቶቻቸውን እና አልባሳታቸውን በመኪና ጭነው እንደወሰዱባቸው ገልጸው ነበር።
አቡነ እንጦንዮስ 3 ሺህ የሚሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትን ለማባረር ፈቃደኛ ባለመሆናቸውና እንዲሁም የታሰሩ ካህናትም እንዲፈቱ በመጠየቀቻው ለቁም እሥር እንደበቁ ይነገራል።
የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብጹዕ አቡነ ቄርሎስን አምስተኛው ፓትሪያርክ አድርጋ የቀባችው ባለፈው አመት መጨረሻ ነበር።
አንዳንዶች ግን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቀደሞ የተሰየሙ ፓትሪያርክ በህይወት አስካሉ ድረስ አዲስ ጳጳስ መሾም እንደማትፈቅድ በመጥቀስ ትችት ሰንዝረዋል።
በአሜሪካ ተቀማጭነታቸውን ባደረጉት የኮፕቲክ ጳጳስ አቡነ መቃርዮስ የሚመሩት ተከታዮቻቸው መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ ይገባል ሲሉ ከሰዋል።
የኤርትራ መንግሥት ከዚህ በፊት የሚወቀስባቸውን ጣልቃ ገብነትን እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሲክድ ቆይቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኤርትራ መንግሥትን በሃይማኖታዊ ጭቆናዎች ይወቅሳሉ።
አቡነ እንጦንዮስ የመንግሥትን ባለስልጣናትን ጣልቃ ገብነት እና የሰብዓዊ መብትን ረገጣን በመቃወም በበርካታ ዲያስፖራዎች ዘንድ የፅናት ተምሳሌት ተደርገው ተወስደዋል።
በርካቶች ለፓትርያርኩ ኃዘናቸውን በማህበራዊ ሚዲያ እያካፈሉ ነው።
የቀድሞውን ፓትርያርክ ማረፍ አስመልክቶ ከመንግሥት ባለስልጣናት በኩል የተባለ ነገር የለም።
አቡነ እንጦንዮስ ሕምብርቲ የተባለች ከአስመራ ከተማ ወጣ ብላ ያለች ቦታ እንደተወለዱ መዛግብት ያስረዳሉ።