ታንዛኒያ እናት ተማሪዎች ልጆቻቸውን ይዘው መማሪያ ክፍል እንዳይገቡ አገደች

አስናት ጌዲዮን ልጇን ታቅፋ በክፍል ውስጥ
የምስሉ መግለጫ, አስናት ጌዲዮን ልጇን ታቅፋ በክፍል ውስጥ

ነፍሰጡር ተማሪዎችን ከትምህርት ቤት የሚያግደው እና ከወሊድም በኋላ ወደ ትምህርት እንዳይመለሱ የሚከለክለው መመሪያዋን በቅርቡ የሻረችው ታንዛኒያ እናቶች ልጆቻቸውን ይዘው ወደ መማሪያ ክፍል መግባት እንደማይችሉ አስታወቀች።

የታንዛኒያ የትምህርት ሚኒስቴር ነፍሰጡርና ወላድ ተማሪዎችን የሚመለከተውን መመሪያውን በቅርቡ ቢሽርም እናቶች ልጆቻቸውን ይዘው ው ትምህርት ቤት እንዳይመጡ አዟል።

የትምህርት ሚኒስትሩ አዶልፍ ማኬንዳ ተማሪዎች ከወለዱ በኋላ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ፈቅደናል ማለት ልጆቻቸውን ወደ መማሪያ ክፍል ይዘው መምጣት ይችላሉ ማለት አይደለም ብለዋል።

ሚኒስትሩ ይህን አስተያየት የሰጡት በታንዛኒያ በምቤያ ግዛት አንዲት ትምህርቷን እየተከታተለች ያለች እናት በዚህ ሳምንት የአራት ወር ልጇን ወደ ትምህርት ቤት እንድታመጣ እንደተፈቀደላት የሚያትት ዘገባ ቢቢሲ መስራቱን ተከትሎ ነው።

በዚህ የቢቢሲ ዘገባ የ19 ዓመቷ አስናት ጌዲዮን ልጇን ታቅፋ በመማሪያ ክፍል ውስጥ ትምህርቷን ስትከታተል ያሳያል። ተማሪዋ ልጇን በቤት ውስጥ የሚንከባከብላት ሰው ባለመኖሩ ይህንን ለማድረግ መገደዷንም ለቢቢሲ ተናግራለች።

ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ማኬንዳ በክፍል ውስጥ ሕፃናት ይዞ መገኘት ሌሎች ተማሪዎችን ስለሚረብሽ ይህንን ማድረግ እንዳማይፈቀድ ገልጸዋል።

በታንዛኒያ ያረገዙ ተማሪዎች ከትምህርት ይታገዱ የነበረ ሲሆን ከወሊድ በኋላም ወደ ትምህት ቤት እንዲመለሱ አይፈቀድላቸውም ነበር።

ላለፉት 19 ዓመት የተተገበረው ይህ መመሪያ ከወራት በፊት የተሻረ ሲሆን በርካታ እናት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ምክንያት ሆኗል።

ትምህርት የሚከታተሉ እናቶችን ወደ ትምህርት ሲመለሱ ልጆቻቸውን በምን መልኩ ይጠብቁ በሚለው ሃሳብ ዙሪያ የትምህርት ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ እንዲያቀርቡ በቢቢሲ ዘገባ ላይ የቀረበችው እናት መነሻ ሆናለች።

እንደ አስናት ጌዲዮን አማራጭ ለሌላቸው እናቶች የሕጻናት ማቆያ ማዕከላት እንዲቋቋሙ ሐሳብ መቅረቡን አንድ የትምህርት ባለሙያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።