ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የማይልኩ ታንዛኒያውያን ወላጆች እስር እንደሚጠብቃቸው ተነገረ

በታንዛኒያዋ ዶዶማ ከተማ የሚገኙ ወላጆች ከሚቀጥለው ሳምንት አንስቶ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የማይልኩ ከሆነ እስር እንደሚጠብቃቸው አንድ ባለሥልጣን አስጠነቀቁ።
ይህንን ያሉት የሚጠበቀውን ያህል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶች ባለመምጣታቸው የተቆጡት የዋና ከተማዋ ዶዶማ እና በዙሪያዋ ያሉ አካባቢዎች ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አንቶኒ ምታካ ናቸው።
ዋና አስተዳዳሪው አርብ እለት በከተማዋ በሚገኝ በአንድ ትምህርት ቤት ተገኝተው ጉብኝት ባደረጉበት ጊዜ በተመለከቱት ዝቅተኛ የተማሪዎች ቁጥር ተቆጥተው ነው በወላጆች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የተናገሩት።
አንቶኒ ምታካ በጎበኙት ትምህርት ቤት ውስጥ በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት ከሚጠበቅባቸው 165 ተማሪዎች መካከል በባለሥልጣኑ ጉብኝት ወቅት የተገኙት 67 ብቻ ነበሩ።
በዚህም ሳቢያ ስሜታዊ የሆኑት ዋና አስተዳዳሪው ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወላጆች ሁሉንም ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ እንዲያደርጉ ካልሆነ ግን ለእስር እንደሚዳረጉ በቁጣ ተናግረዋል።
ወላጆችን "እናንተ ልጆቻችሁን ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ሳታደርጉ እኔ የተሟሉ የመማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት አልችልም። ከዚህ በኋላ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ጀምሮ በየቤቱ እየዞርኩ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ሳይልኩ የቀሩ ወላጆች እንዲታሰሩ አደርጋለሁ" ብለዋል።
የዶዶማ ግዛት አስተዳዳሪው ከዚህ በኋላ ከትምህርት ቤት የሚቀሩ ተማሪዎችን ጉዳይ በተመለከተ ትዕግስት እንደማይኖራቸው በመግለጽ እርምጃ እንደሚወሰዱ አስጠንቅቀዋል።
በታንዛኒያ አዲሱን የአውሮፓውያን ዓመት መግባት ተከትሎ የተጀመረው የትምህርት ዘመን ሁለት ሳምታት ያስቆጠረ ቢሆንም የሚጠበቀውን ያህል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶች እየመጡ አይደሉም ተብሏል።
ለዚህም እንደምክንያት የሚነገረው አንዳንድ ወላጆች ኑሯቸውን ለመደጎም ልጆቻቸውን በተለያዩ ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ በማድረጋቸው ወይም በሰው ቤት ውስጥ ተቀጥረው እንዲሰሩ በማድረጋቸው ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።












