ከስድስት ዓመታት በላይ በአማፂያን ታግተው የነበሩት ኮሎምቢያዊት ለፕሬዚዳንትነት ሊወዳደሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞዋ የኮሎምቢያ ሴናተርና ከ20 አመታት በፊት በግራ ክንፍ አማፂያን ታግተው የነበሩት ኢንግሪድ ቤንታኮርት ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ አስታወቁ።
ኢንግሪድ በአውሮፓውያኑ 2002 በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ቅስቀሳ እያደረጉ በነበረበት ወቅት በፋርክ አማፂያን ተወስደው ከስድስት ዓመታት በላይ ታግተው ቆይተዋል።
ፖለቲከኛዋ በመጪው ግንቦት ወር የሚደረገውን ምርጫ ካሸነፉ ሙስናን እና ድህነትን ለመቅረፍ ቃል ገብተዋል።
"በአሁኑ ወቅት ልወዳደር የመጣሁት የጀመርኩትን ለመጨረስ ነው" ሲሉ በሃገሪቱ መዲና ቦጎታ ላሉ ደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።
"እኔ ፊታችሁ የተገኘሁት ፍትህ የማያገኙ 51 ሚሊዮን ኮሎምቢያውያንን መብት ለመጠየቅ ነው፤ ምክንያቱም የምንኖረው ወንጀለኞችን ለመሸለም በተዘጋጀ ስርአት ውስጥ ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።
የፋርክ አማፅያን ከ50 ዓመታት በላይ ከኮሎምቢያ መንግሥት ጋር ደም አፋሳሽ ጦርነት ያካሄዱ የማርክሲስት ቡድን ነበሩ። በመጨረሻም በአውሮፓውያኑ 2016 የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ተደረሰ።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ መጪው ሰኔ ለሚደረገው ምርጫ ከ20 በላይ እጩዎች እንደሚወዳደሩ ታውቋል።
የቦጎታ የቀድሞ ከንቲባ እና ኤም- 19 የተባለው የአብዮታዊ ሽምቅ ተዋጊ ቡድን አባል የነበሩት ጉስታቮ ፔትሮ በአሁኑ ጊዜ በህዝብ የምርጫ አስተያየት መስረት በግንባር ቀደምትነት እየመሩ ነው።
በርካታ ኮሎምቢያውያን በአሁኑ ጊዜ አገሪቱን እየመሩ ካሉትና ተወዳጅነታቸው እያሽቆለቆለ ከመጣው የቀኝ ክንፍ ፖለቲከኛው ፕሬዚዳንት ኢቫን ዱክ የተሻለ አማራጭ አድርገው ያዩዋቸዋል ጉስታቮ ፔትሮን።
ፕሬዚዳንት ኢቫን ዱክ በጊዜ ገደብ ምክንያት በዘንድሮው ምርጫ መወዳደር አይችሉም።
ኢንግሪድ ቤንታኮርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነት ቢኖራቸውም በአውሮፓውያኑ 2008 በኮሎምቢያ ወታደራዊ ሃይሎች አማካኝነት ከተለቀቁ በኋላ ድምፃቸው አይሰማም። በአሁኑ ወቅትም ፓርቲያቸውን ኦክስጅንን ጨምሮ በተዋቀረው ሴንትሪስት በተባለው ጥምረት እጩነትን ለማሸነፍ ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ ምርጫ ሁለት ወራት ብቻ በቀረውና ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በግጭት ሰለባ ሆነው በመንግሥት በተመዘገቡባት ሀገር ራሳቸውን እንደ አስታራቂ እጩ አድርገው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
ኢንግሪድ ቤንታኮርት በፋርክ አማፂያን የታገቱት ሳን ቪሰንቴ ዴል ካጉዋን በምትባል ከተማ የነበራቸውን የምርጫ ቅስቀሳ አጠናቀው ሲመለሱ መንገድ ላይ ነው።
በኮሎምቢያ ጫካ ውስጥ በቆዩባቸው ስድስት ዓመታት ውስጥ በአጋቾቻቸው ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል።
በፋርክ አማፂያን ውስጥ የነበሩ ሰርጎ ገብ የኮሎምቢያ ጦር አባላትም ተቀናጅተው ነው በአውሮፓውያኑ 2008 ያስለቀቋቸው።
ከተለቀቁም በኋላ በርካታ አመታትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው በፈረንሳይ ነው የኖሩት።
የፋርክ አማጽያን ከ50 ዓመታት በላይ ከመንግሥት ጋር ባደረጉት የእርስ በርስ ጦርነት ከ200 ሺህ ሰዎች በላይ ተገድለዋል።
ቡድኑ በአውሮፓውያኑ 2016 የሰላም ስምምነት ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ተፈራርመው የተወሰኑት ወደ ፓርላማ ሲገቡ የቀሩት ደግሞ በጦርነቱ ቀጥለዋል።












