ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአፋር እና በትግራይ አዋሳኝ አካባቢ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ተነገረ
በአፋር እና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች ላይ ከቀናት በፊት የተኩስ ለውውጥ እንደነበረ ተነገረ።
በአዋሳኝ የድንበር አካባቢዎቹ ላይ ለደረሱት ጥቃቶች የአፋር ክልል መንግሥት እና ህወሓት አንዳቸው ሌላኛውን ተጠያቂ እያደረጉ ነው።
በተኩስ ልውውጡ በንጹሃን ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ሁለቱም ወገኖች ገልጸዋል።
የአፋር ክልል ህወሓት በአፋር አብኣላ በኩል በንጹሃን ላይ ጥቃት እያደረሰ ነው ሲል ከሷል።
ህወሓት በበኩሉ የአፋር ልዩ ኃይል 'በሕዝባችን ላይ ተከታታይ ጥቃቶችን እየሰነዘረ ነው' ብሏል።
14 ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት የትግራይ ኃይሎች ይዘዋቸው ከነበሩት አፋር እና አማራ ክልል ቦታዎች ከወጡ በኋላ ጋብ ብሎ የቆየ ቢሆንም የፌደራሉ መንግሥት በሚፈጽማቸው ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶች በርካቶች ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል።
ይህ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ስለመቅጠፉ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩት አፈናቅሏል። ከዚህ በተጨማሪም ይህ ጦርነት ከፍተኛ የሆኑ የሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
የአፋር ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ጽ/ቤት ትናንት ጥር 08/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ የትግራይ ኃይሎች "በሰላም ወዳዱ የአፋር ሕዝብ ላይ በድጋሚ እያካሄደ ያለውን" ጥቃት በአስቸኳይ ማቆም አለበት ብሏል።
ክልሉ ህወሓት በኪልበቲ ረሱ (ዞን ሁለት) በአብአላ በኩል ከታኅሣሥ 10 ጀምሮ በተከታታይ እየተኮሰ ባለው ከባድ መሳሪያ ንጹሃን ዜጎችን ጉዳት እየደረሰባቸው ነው ብሏል።
ህወሓት በኪልበቲ ረሱ አብአላ እና መጋሌ በኩል በተለይ አርብ እና ቅዳሜ በፈጸመው የከባድ መሳሪያ ድብደባ በበርካቶች ላይ ጉዳት መድረሱን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በጥቃቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን እንዲሁም በንብረት ላይ ውድመት መድረሱን የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት በመግለጫው አትቷል።
ህወሓት በበኩሉ ትናንት ባወጣው መግለጫ የአፋር ልዩ ኃይል በትግራይ ሕዝብ ላይ ጥቃቶችን እያደረሰ ነው ብሏል።
ከትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ ፖስት ተሰጠ በተባለው መግለጫ፤ የአፋር ልዩ ኃይል ቅዳሜ ጥር 07/2014 ዓ.ም. ምላዛትን እና ዳንደን በተባሉ አከባቢዎች ጥቃት ፈጽሟል ተብሏል።
ኮማንድ ፖስቱ ተከፈተብኝ ያለውን ጥቃት በወሰደው የአጸፋ ምላሽ ጥቃቱን መመከት መቻሉን አስታውሶ፤ መሰል ጥቃቶች እንዲቆሙ፤ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች ጫና እንዲያሳድሩ አሳስቧል።
ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ከአንድ ዓመት በላይ የሆነው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ከተስፋፋ በኋላ ከኅዳር ወር ወዲህ ጋብ ብሎ ቆይቷል።
ነገር ግን በአማራ፣ በትግራይ እና በአፋር አዋሳኝ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ግጭቶች እንዳሉ ቢሰማም የመገናኛ አገለግሎቶች በመቋረጣቸው ያለውን ሁኔታ ለማወቅ አስቸጋሪ ሆኗል።
የፌደራል መንግሥቱ ቀደም ሲል በህወሓት ተይዘው የነበሩ የአፋርና የአማራ አካባቢዎችን በቁጥጥሩ ስር ካስገባ በኋላ ወታደራዊ ዘመቻውን ወደ ትግራይ ለመቀጠል እንደማይፈለግ በማሳወቅ ሠራዊቱን ባለበት እንዲቆይ ማዘዙ ይታወሳል።