ሞቃዲሾ ውስጥ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተዘገበ

የቦምብ ፍንዳታው የደረሰበት ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቦምብ ፍንዳታው የደረሰበት ስፍራ

በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ውስጥ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የነፍስ አድን ሠራተኞች አስታወቁ።

ፍንዳታው በደረሰበት ስፍራ በቡድን ሲጓዙ የነበሩ የተሽከርካሪዎች አካላት በየቦታው ተበታትኖ የተገኘ ሲሆን፣ በአካባቢው ያሉ ህንጻዎች ክፉኛ ተጎድተው መንገዱ በፍርስራሽ መሸፈኑ ተገልጿል።

በከባድ ጥበቃ ስር ከሚገኘው ከሞቃዲሾ አየር ማረፊያ ብዙም ሳይርቅ የደረሰው ፍንዳታ ከመኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ አማካይነት እንደሆነ የከተማዋ የአምቡላንስ አገልግሎት ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

አስካሁን ይህንን ከባድ የፍንዳታ ጥቃት የፈጸመው ቡድን ማን እንደሆነ ባይታወቅም ሳይቆይ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው እስላማዊው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ በተደጋጋሚ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃቱ ሲፈጽም ቆይቷል።

ከታጣቂው ቡድን በተጨማሪ በሶማሊያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል ያለው የሥልጣን ፉክክርና አለመግባባት ባላፉት ሳምንታት ውስጥ አገሪቱን ውጥረት ውስጥ ከቷት ቆይቷል።

በፕሬዝዳንቱና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል ለወራት የዘለቀው አለመግባባት ከሳምንት በፊት ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌን ከሥልጣን ማገዳቸውን ተከትሎ የበለጠ ተባብሶ ቀጥሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ ባለመቀበል በሥራቸው የቀጠሉ ሲሆን ሁለቱን ባለሥልጣንና ለማስማማት ጥረቱ እንደቀጠለ ነው።

በሶማሊያ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ምርጫ ከተራዘመ በኋላ በአገሪቱ ባሉ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለው ቅራኔ የተባባሰ ሲሆን፣ ምርጫው በቅርቡ እደሚካሄድ ይጠበቃል።

ይህ በአገሪቱ ፖለቲከኞች መካከል የእየተካረረ ያለው አለመግባባት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ለታጣቂው እስላማዊ ቡድን አመቺ ሁኔታ በመፍጠር ከፍተኛ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል ስጋት አለ።

አልቃኢዳ ከተባለው እስላማዊ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት አልሻባብ ከዚህ በፊት ለተፈጸሙ ተመሳሳይ የቦምብ ጥቃቶች ኃላፊነቱን መውሰዱ ይታወሳል።

ቡድኑ በሶማሊያ ያለውን ማዕከላዊ መንግሥትን በማስወገድ ጥብቅ አስላማዊ ሕግጋትን ተግባራዊ ለማድግ ይፈልጋል። ከዚህ በፊት አልሻባብ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና ኢላማዎች ላይ የፈጸመ ሲሆን ሰላማዊ ሰዎችም የጥቃቱ ሰለባዎች ናቸው።

ከዚህ ባሻገርም ቡድኑ በሶማሊያ ውስጥ በተሰማሩት የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ላይ ጥቃቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።