ዴንማርክ በቁጥጥሯ ሥር የነበሩ ተጠርጣሪ የባሕር ላይ ወንበዴዎችን በነጻ ለቀቀች

እቃ ጫኝ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, DANISH ARMED FORCES

በዴንማርክ የጦር መርከብ በምዕራብ አፍሪካ የባሕር ዳርቻ ለስድስት ሳምንታት ታስረው የነበሩና የባሕር ላይ ወንበዴ እንደሆኑ የተጠረጠሩ ሦስት ግለሰቦች ተለቀቁ።

በአነስተኛ ጀልባ ተጭነው የተለቀቁት ሦስቱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት በኅዳር ወር በጊኒ ባሕረ ሰላጤ ከተደረገ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ በኋላ ነበር።

የዴንማርክ ጦር ኃይሎች ተጠርጣሪዎቹ በተያዙበት ቀጠና ውስጥ የባሕር ላይ ወንበዴዎች ናቸው ተብለው የተያዙትን ግለሰቦች የሚረከብ አገር ማግኘት አልቻልኩም ብሏል።

በዚህም ምክንያት በቁጥጥር ሥር የነበሩት ተጠርጣሪዎች በናይጄሪያ አቅራቢያ ባለ የውሃ አካል በኩል ከበቂ ምግብ እና ነዳጅ ጋር ወደ ባሕር ዳርቻው እንዲሄዱ ተወስኗል።

እንደ ዴንማርክ ባለሥልጣናት ገለጻ ከሆነ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በኮንቴይነር ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ከፈጸሙ እና የተኩስ ልውውጥ ከተደረገ በኋላ ነው።

ከጥቃት አድራሾቹ መካከል አራቱ በዴንማርክ ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን ሌሎች አራት ሰዎች ደግሞ በዴንማርክ የባሕር ኃይል መርከብ ውስጥ እዲታሰሩ ተደርጓል። የዴንማርክ ወታደሮች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ተከሰው የነበረ ቢሆንም ክሱን አስተባብለዋል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዱ እግሩ ወደ ተቆረጠበት ጋና ከተወሰደ በኋላ የግድያ ሙከራ ወንጀል ክስ ለመመስረት ወደ ዴንማርክ ተዛውሯል።

የዴንማርክ የፍትህ ሚኒስቴር በባሕር ላይ ወንጀል ከፈጸሙ በኋላ በሰላም መልቀቅ የሚቻል አልመሰላቸውም ነበር ብለዋል። ሦስቱ ተጠርጣሪዎች ላይ የነበረው ክስም መቋረጡን ጠበቆቻቸው አረጋግጠዋል።

ነገር ግን በእስር ላይ ያለው ተጠርጣሪ ጠበቃ የሆኑት ቢርጊት ስኪጆት በእሱ ላይ ክስ ለመመስረት መወሰኑን በመተቸት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን "አራቱን ሰዎች በእኩል ዓይን አለማስተናገድ ትክክል ሊሆን አይችልም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ዴንማርክ የባሕር ላይ ወንበዴ ተጠርጣሪን ወደ ግዛቷ ስታስገባ ይህ የመጀመሪያዋ ነው። አገሪቷ በጊኒ ባሕረ ሰላጤ ዳርቻ ከሚገኙ አገሮች ጋር የባሕር ላይ ወንበዴዎችን አሳልፎ መስጠትን በተመለከተ ምንም ዓይነት ስምምነት የላትም።

ነዳጅ እና ጋዝ የጫኑ ታንከሮች የሚመላለሱበት የጊኒ ባሕር ለተወሰኑ ዓመታት የባሕር ላይ ወንበዴዎች መናኸሪያ ሆኖ ቆይቷል።

የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የላላ ሕግ ማስከበር እና ድህነት በአካባቢው የባሕር ላይ ዝርፊያ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል።

ነገር ግን በአከባቢው ያለውን ጸጥታ ለማጠናከር የአገራት ባለሥልጣናት እና የውጭ የባሕር ኃይል መርከቦች የጋራ ጥረት እያደረጉ ነው።