ቻይና ለአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ልትሾም መሆኑን አስታወቀች

ቻይና በቀጠናው የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን በመፍታት በኩል አስተዋጽኦ ለማበርከት ለአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ልትሾም መሆኑን አሳወቀች።

ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች አንዷ በሆነችው ኤርትራ የነበራቸውን የሁለት ቀናት ጉብኝት በትናንትናው ዕለት አጠናቀው ወደ ኬንያ ያቀኑት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በዛሬው ዕለት ታኅሣሥ 28/2014 ነው ይህንን እቅድ አስመልክቶ የተናገሩት።

በኬንያዋ የባሕር ዳርቻ ከተማ ሞምባሳ ውስጥ በዛሬው ዕለት በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም "ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና መጫወታችንን እንቀጥላለን" በማለት ዋንግ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ቀንድ አገራት የራሳቸውን እጣ ፈንታ እንዲወስኑ እና የሰላም ጉባዔ እንዲጠሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጨምረው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሚኒስትሩ በምሥራቅ አፍሪካ ሦስት አገራት ጉብኝት እያደረጉ ሲሆን እስካሁንም ባለው ከኤርትራ ባለሥልጣናት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት መፍትሔ እንዲያገኝ ሚና አላት ከምትባለው ኬንያ አመራሮች ጋር የተነጋገሩ ሲሆን በመቀጠልም ወደ ወደ ሕንድ ውቅያኖሷ ደሴት ኮሞሮስ ያቀናሉ ተብሏል።

ሚኒስትሩ በኤርትራ በነበራቸው ቆይታም በምዕራባውያን ዘንድ በተገለለችው ኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ አውግዘዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ የአሜሪካ መንግሥት በአራት የኤርትራ ተቋማትና በሁለት ኤርትራውያን ላይ በያዝነው ዓመት ማዕቀብ ጥሏል።

ማዕቀቡ የኢትዮጵያን መረጋጋትና አንድነት እያናጋ ነው ባለው ቀውስና ግጭት ውስጥ አስተዋጽኦ አላቸው ያላቸውን የኤርትራ ተቋማትና ዜጎችን ኢላማ ያደረገ መሆኑን የአሜሪካ የፌደራል ግምጃ ቤት በወቅቱ አመልክቷል።

ኅዳር ወር መጨረሻ አካባቢ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው የነበሩት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአዲስ አበባ ጉብኝታቸውንም በተመለከተ ቻይና በኢትዮጵያ ላይ ያላትን መተማመን እንደሚያሳይ እና ቻይና ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ያላትን ድጋፍ የሚገልጽ ነው ማለታቸውም የሚታወስ ነው።

ቻይና በቅርብ ወራት በተለይ ደግሞ ከትግራዩ ጦርነት ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ መድረኮች ላይ ድጋፏን ስትገልጽ ቆይታለች።

የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል የሆነችው ቻይና፤ የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ መክሮ የውሳኔ ሐሳብ እንዳያወጣ ሲቃወሙ ከነበሩ አገራት መካከል አንዷ ነች።

የቻይናው ሚኒስትር በቀጣናው የሚያደርጉት ጉብኝት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ከሚያደርጉት ጉብኝት ጋር የተገጣጠመ ሲሆን ፌልትማን በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ለ14 ወራት የዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ጉዳይ ለመምከር ሐሙስ ታኀሣሥ 28/2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ ይገባሉ ተብሏል።

በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ያላት ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እያደገ የመጣው ቻይና፣ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን አለመረጋጋት በተመለከተ ልዩ መልዕክተኛ ለመሰየም ያለት ሐሳብ ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛዋ አገር ያደርጋትል።