ዩኬ ዩክሬንን ከሩሲያ ለመከላከል ወታደሮች የማሰማራት እድሏ አነስተኛ እንደሆነ ተገለጸ

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ብሪታንያ እና አጋሮቿ ዩክሬንን ለመከላከል ወታደሮች የመላክ ዕድላቸው አነስተኛ ነው ሲሉ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የመከላከያ ኃላፊ ተናግረዋል።

"እንልካለን ብለን መሸወድም ሆነ መቀለድ የለብንም" ሲሉ ቤን ዋላስ ለስፔክተር መፅሄት ተናግረዋል።

"ይህንንም ዩክሬናውያን ጠንቅቀው ያውቃሉ" ሲሉ አክለዋል።

ሩሲያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን በዩክሬን ምሥራቃዊ ድንበሮች አቅራቢያ ማስፈሯን ተከትሎ የምዕራባውያን ኃይሎች ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ውጥረቱን እንዲያረግቡ ጠይቀዋል።

ሩሲያ በበኩሏ በዩክሬን ላይ ጥቃት አቅዳለች የሚለውን ጉዳይ አጥብቃ የምትቃወም ሲሆን ከአሜሪካ ጋር አስቸኳይ ውይይት እንዲደረግ ጠይቃለች።

በያዝነው ሳምንት አርብ ዕለት ሩሲያ በአሜሪካ የሚመራው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን አገሮች ድርጅት (ኔቶ) ወታደራዊ ጥምረት በምሥራቅ አውሮፓ በሚገኙ አገራት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ ጥብቅ ገደብ እንዲደረግ ጠይቃለች። ።

ሕብረቱ በመጀመሪያ የተቋቋመው አውሮፓን ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሊደርስባት ከሚችል ሥጋት ለመከላከል ነበር።

የመከላከያ ኃላፊው ከስፔክታተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዩክሬን "የኔቶ አባል አይደለችም ስለዚህ የትኛውም አገር ሩሲያን ለመገዳደር ወታደሮቹን ወደ ዩክሬን የማሰማራት እድል የለውም" ብለዋል ።

"ለዚህም ነው ለፕሬዚዳንት ፑቲን በዩክሬን ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝሩ በማለት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የተቻለንን እያደረግን ያለነው" ያሉት ዋላስ "ሆኖም ይህንን ለመቀልበስ የከፋ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣል ዕድሉ ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

ዋላስ ቀደም ሲል አገራቸው "ከዩክሬን ሕዝብ ጋር እንደምትቆም እና እነሱን ለመደገፍ ቆርጣ እንደተነሳች" ተናግረው ነበር።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ፑቲን በቀጣናው ላይ "ብጥብጥ ካስነሱ" የአጸፋ ምላሽ ይኖረዋል በሚል አስጠንቅቀው ነበር።

ዩክሬን ከአውሮፓ ሕብረት እና ከሩሲያ ጋር ድንበር ትጋራለች ፣ ነገር ግን እንደ ቀድሞ የሶቪየት ኅብረት አባልነቷ ከሩሲያ ጋር በበለጠ ጥልቅ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ትስስር አላት።

ሩሲያ ዩክሬን ወደ ኔቶ ለመቀላቀል ፍላጎት በማሳየቷ እየተነኮሰችኝ ነው ስትል ከሳለች።

ሩሲያ አርብ ዕለት ይፋ ባደረገችው ውሳኔ ከሶቪየት ኅብረት ውድቀት በኋላ ኔቶን የተቀላቀሉ አገራት ወታደሮቻቸውን ወይም የጦር መሣሪያዎችን ለሩሲያ አስጊ ናቸው በሚባሉ አካባቢዎች እንዳያሰማሩ የሚጠይቁትን ጨምሮ በርካታ ሥር ነቀል ማሻሻያዎችን አስቀምጣለች።