ካናዳ ለቀደምት ህዝቦች ልጆች ካሳ የሚሆን 40 ቢሊዮን ዶላር ልትሰጥ ነው

ካናዳ በአስገዳጅ አዳሪ ትምህርት ቤት ተወስደው መገለልና አድልዎ ላስተናገዱ የቀደምት ህዝቦች ልጆችና ቤተሰቦች እስከ 40 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ለመስጠት ቃል ገብታለች።

በመስከረም ወር ላይ የአገሪቱ አንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀደምት ህዝቦች ልጆች የነበሩባቸው አዳሪ ትምህርት ቤቶች መንግሥት ሆን ብሎ አገልግሎት እንደነፈጋቸው በአውሮፓውያኑ 2016 የተላለፈውን ብይን አፅድቆታል።

በዚህም ውሳኔ መስረት ከአውሮፓውያኑ 2006 በኋላ በነዚህ ስፍራዎች ለነበሩ እያንዳንዱ ልጅ 40 ሺህ ዶላር እንዲከፈላቸው አዟል።

መንግሥት ውሳኔውን በጸጋ እንደማይቀበለውና ይግባኝ እንደሚጠይቅም አስታውቆ ነበር።

ነገርግን በቀድሞ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ከ1 ሺህ 100የሚበልጡ ምልክት የሌላቸውና በመቶዎች የሚቆጠሩ ህፃናትን አፅም የያዙ የጅምላ መቃብር ከተገኙ በኋላ ከህዝቡ ወቀሳን እያስተናገደ ይገኛል።

መቃብሩ የተገባቸው ስፍራዎች በዋነኝነት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይመሩ የነበሩና የካናዳ ቀደምት ህዝቦችን ወደ ነጭ ባህል ለማላመድ በሚል የተከፈቱ አስገዳጅ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ናቸው።

እነዚህ ትምህርት ቤቶችም በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ነበሩ።

እስከ አውሮፓውያኑ 1996 ድረስ የቀጠሉት እነዚህ ትምህርት ቤቶች የቀደምት ህዝቦችን ልጆች ከቤተሰቦቻቸው ለይቶ በመንጠቅ ወደነዚህ አዳሪ ትምህር ቤቶች ያስገቧቸው ነበር። በርካታ ህፃናትም የምግብ እጥረትን ጨምሮ ከፍተኛ ድብዳባና እና ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

በትምህርት ቤቱም ህፃናቱ የራሳቸውን ባህልና አፍ መፍቻ ቋንቋቸውን እንዲረሱና የክርስትና እምነትን እንዲቀበሉ ይደረጉ ነበር። ህፃናቱንም ከነጮች ባህል ጋር ለማዋሃድ ሲባል በርካታ ግፎች ተፈፅመዋል።

ማክሰኞ በይፋ ይገለጻል ተብሎ የሚጠበቀው የመንግሥት የካሳ መጠን በአውሮፓውያኑ 2016 ላይ ፍርድ ቤት ለቀረቡ ክሶች እንዲሁም የቀደምት ህዝቦች ህፃናትን ደህንነትና ስርዓት ለመደጎም የሚውል የረዥም ጊዜ ማሻሻያዎችን እንደሚውል ሲቢሲ የተባለው የዜና ምንጭ ለሲቢሲ ተናግሯል።

"ገንዘብ ፍትህ ማለት አይደለም፣ነገር ግን ወደፊት በፈውስ ጎዳና ላይ መሆናችንን ያሳያል" ሲሉ የቀደምት ህዝቦች ምክር ቤት ብሄራዊ ሃላፊ የሆኑት ሮዝአኔ አርኪባልድ ተናግረዋል።

"የታቀደው የካሳ ፓኬጅ መጠን ምን ያህል ልጆቻችን ከቤተሰቦቻቸው እና ከማህበረሰቡ እንደተነጠቁ ማሳያ ነው" ሲሉ አክለዋል።

ከአውሮፖውያኑ 1863-1996 150 ሺህ የሚሆኑት እነዚህ ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው በአስገዳጅ ሁኔታ ተወስደው በነዚህ ትምህርት ቤቶች ይማሩ ነበር።.